
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሰርከስ በኢትዮጵያ የ70 ዓመት ዕድሜ ያለው የክዋኔ ጥበብ ዘርፍ ነው፤ ነገር ግን እንደ ሌሎች የሲቪክ የሙያ ማኅበራት በማኅበር ተደራጅቶ ሙያውን እያሳደገ አልነበርም፡፡ የሰርከስ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን ሙያውን ማሳድግ የሚችሉበትና ለሙያው ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስችል የተደራጀ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉበት የአማራ ክልል ሰርከስ ማኅበር በባሕር ዳር ዛሬ ተመሥርቷል፡፡
በምሥርታው የፕሮግራሙ አስተባባሪ አርቲስት ውዴ ዘለቀ እንደተናገሩት የአማራ ክልል ሰርከስ ባሕር ዳር እንዲመሠረት ብዙ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የማኅበሩ መመሥረት ደግሞ በአገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቶት እንቅስቃሴ ለማድረግ ይጠቅማል›› ብለዋል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ በሚሠራው ሥራ ጉድለቶችን በተናጥል ከመጠቅ በኅብረት ለመጠየቅ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም ወይዘሮ ውዴ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል ኢንዱስትሪ ባለሙያ አቶ አፈወርቅ ተፈራ እንደተናገሩት ደግሞ ዛሬ የተመሠረተው የክልሉ ሰርከስ ማኅበር ባሕል እንዲተዋወቅ፣ ዘመኑ በሚፈልገው በቴክኖጂ እንዲደገፍ እና በዓለም አቀፍ ዘርፍ ለማዘመን በማኅበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ስፊ ተቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮም የሰርከስ ጥበብ ባለሙያዎችን በመመደብ፣ ሰርከስ በጥበብ አደረጃጀት እንዲታቀፍ እና የአደረጃጀት መመሪያ ሰነድ እንዲዘጋጅለት ማደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በቢሮ ከባሕል ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረትም ብቃት ላላቸው ባለሙያዎች የሙያ ብቃት በመስጠት ክልሉ በሰርከስ ዘርፍ ዕውቅና እንዲያገኝ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
ከምሥረታ በኋላ ለሙያ ማኅበሩ ሕጋዊ ሰነድ ተስጥቶ ‹የአማራ ክልል ሰርከስ ማኅበር› በመሆን በክልሉ ሙሉ ዕውቅና ስለሚያገኝ እንደማንኛውም ሲቪክ ማኅበር የትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት እንደሚችሉም አብራርተዋል፡፡
በምሥረታው ከተሳተፉ ባለሙያዎች መካከል ተማሪ ሠላማዊት ተካልኝ ሰርክስ እንደ አንድ ኪነ ጥበብ ዘርፍ ዕውቅና ተስጥቶት ማኅበሩ በመደራጀቱ ሙያቸውን ለማሳደግ እንደሚጠቅም ተናግራለች፡፡ ‹‹ሙያው በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ፣ በጤና እና በኢኮኖሚ ራሳቸውን ለመደገፍ ይጠቅማል›› ብላለች ተማሪ ሠላማዊት፡፡ ከዚህ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው የሰርከስ ትዕይንት ተሳጥፋ ጥሩ ሥራ ማሳየት እንደቻለች የተናገረችው ሠላማዊት ወደፊት በሚደረጉ ውድድሮች ደግሞ በማኅበሩ በኩል ዕውቅና አግኝታ ለመሳተፍ አቅዳለች፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው