
ባሕር ዳር:መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለ2016/17 የእርሻ ወቅት የሚሆን የመነሻ ዘር ብዜት ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የዘር አምራች ድርጅቶች ጋር ኮንትራት ተዋውሎ የመነሻ ዘር እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከፌደራል እና ከክልል የመንግሥት እንዲሁም የግል ዘር አባዥዎችና የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር በገባው ውል መሰረት ነው ኢንስቲትዩቱ የመነሻ ዘር ብዜቱን እያዘጋጀ ያለው፡፡
የመነሻ ዘር ብዜት ከሚቀርብበት አንድ ዓመት ቀድሞ ውል እደሚገባ እና የመነሻ ዘር አቅርቦቱን መነሻ በማድረግ በኩባንያዎቹ በኩል የተመሰከረለት ዘር እንደሚመረት አስገንዝበዋል፡፡
በመስኖ እየተባዛ ያለውን የስንዴን መነሻ ዘር አቅርቦት ሳይጨምር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የተጠየቀውን 80 በመቶ ያህል የመነሻ ዘር ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ላይ ማለትም በብዕር እና አገዳ እህል ( የስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ጤፍ)፣ በጥራጥሬ (ባቄላ፣ አኩሪአተር፣ ሽምብራ፣ ማሾ፣ ምስር፣) እዲሁም በቅባት እህሎች (ሰሊጥ፣ ኑግ) መነሻ ዘር ለማቅረብ ውል መገባቱን አስታውሰዋል፡፡

በጠቅላላው 2 ሺህ 373 ኩንታል ቅድመ መስራች ዘር በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለማቅረብ ውል ከተገባው ውስጥ ከ1 ሺህ 900 ኩንታል በላይ እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ክልሎች የራሳቸውን የመነሻ ዘር አቅርቦት በራሳቸው እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችል ስልት ተቀይሶ ያልተማከለ የአራቢ ዘር ብዜት አሰራር በመዘርጋት ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ክልል የግብርና ምርምር ተቋማት አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!