‹‹ኪነ ጥበብ በመንግሥት ተጨፍልቋል፡፡›› አርቲስት ሽመልስ አበራ

348

‹‹ኢትዮጵያ ረጅም ዕድሜ ያላት እናት ናት ‹በዛችሁብኝ ተበታተኑ› አላለችምና ሁሉም መልካም እናቱን ማስከፋት አይገባውም፡፡›› ገጣሚና ተዋናይ የዱርፍሬ ይፍሩ

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) ጥበብ በቤቷና በባለቤቷ እየደመቀች ነው፤ ደራሲያን በድርሰታቸው፣ ድምፃውያን በጉሮሯቸው፣ የሙዚቃ ተጫዋቾች በመሣሪያቸው፣ ተወዛዋዦች በትክሻና በአንገታቸው፣ አርበኞች በጦር ሜዳ ገድላቸው፣ የሃይማኖት አባቶች በፆምና ጸሎታቸው አለፍ ሲልም በስብከታቸው ኢትዮጵያውያንን አስደምመዋል።

‹‹እንኳን ሐበሻ ባለቤትዬው፤
ጣልያንም ቀና አንድቀን ባዬው›› የተባለለት ጀግና የተፈጠረበት ይኼው የአማራ ክልል ነው። ላልይበላንና ውቅር መስቀለ ክርስቶስን የጠረበ፣ ፋሲልን የገነባ፣ የጠና ገዳማትንና አድባራት የደበረ፣ የጎጄ መስጂድን የገነባ፣ ብራና ፍቆ ቀለም በጥብጦ ታሪክን የዘከረ፣ ጠላት ሲመጣ በጦር በጋሻ መክቶ ያሳፈረና ያባረረ ይኼው ደግና ጀግና ከሌሎች ጀግኖች ጋር ሆኖ ነው። አማራ ክልል ውስጥ የሌለው የለም ብቻ ነው።

ሀገር መገንባት ታሪክ መሥራት ይችልበታል፤ የተራበ ያጎርሳል፤ የታረዘ ያለብሳል፤ የተጠማ ያጠጣል፤ የታሠረ ያስፈታል። በአማርኛ ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› በአዊኛ ‹‹አዲናስ›› በኽምጠኛ ‹‹ወዝ ዲግዝ ተትርነት›› በኦሮሚኛ ‹‹በገ ነጋን ዱፈተን›› እያለ እንግዳን ሲቀበል ያውቅበታል። ከጎንደር ሩዙን፣ ከጎጃምና ከሸዋ ዳጉሳና ጤፉን፣ ከወሎ ጭሱን እና ሀጃውን እያመጣ በፍቅር ያቀማጥላል፤ አማራ።

በኪነ ጥበቡም ዝናው ከዓለም እስከ ዓለም ናኝቷል። እነማን በዚህ ክልል ውስጥ በቀሉ የሚለውን ጽፌ ላልጨርሰው አልጀምረውም፤ ግን ለቁጥር የሚታክት ደራሲ፣ ከያኒ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ ተወዛዋዥ፣ የቅኔ አመስጣሪ፣ ታሪክ ሠሪና ዘካሪ … የጥበብ ሰው ከዚሁ ክልል ወጥቷል ። ባለተመቸ ወቅት፣ በቸገረ ዘመንም ሆነው ብቃታቸውን ለዓለም አደባባይ አቅርበዋል። የሚገናኙበት መድረክ አጥተው ለዘመናት በየፊናቸው ሲጠበቡ ኖረው እነሆ ዛሬ በአንድ ጥላ ስር ተገናኝተው በጥብብ ልብ ሊሰርቁ፣ለሠላም ዘብ ሊቆሙ፣ ሀገር ሊያቆሙ በባሕር ዳር እየመከሩ ነው፤ የኪነ ጥበብ ልሂቃን።

በመድረኩ የታደሙ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ሐሳብ ሰጥተዋል። አርቲስት ሽመልስ አበራ ‹‹ኢትዮጵያ አሁን ሀይ ባይ ያጣች፤ አንድ ጎረምሳ ሰውን የሚነዳበት እና ሀገርን የሚያምስባት ሆናለች። ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ባለባት ሀገር በልቶ ማደር አስቸጋሪ በሆነባት ምድር ወጥቶ መግባትም አሳሳቢ የሆነባት ሀገር ናት›› ብሏል።

አርቲስቱ መንግሥት ኪነ ጥቡን ለዝግጅት ማድመቂያ ካልሆነ በስተቀር ለሀገር ግንባታ፣ ሠላም፣ አንድነት እና ፍቅር እንዳልተጠቀመበትም ተናግሯል ። ‹‹ኪነ ጥበብ በመንግሥት ተጨፍልቋል›› ነው ያለው። ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው አማራና ኪነ ጥበብ ውይይት መልካም መሆኑን ገልጾ ከመድረክ ማሳለፍ ከተቻለ ከፍ ወደላ ደረጃ መሸጋገር እንደሚቻልም አመላክቷል ።

ማንኛውም የኪነ ጥበብ ባለሙያም የክልሉን ባሕል፣ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ያበረከተውን አስተዋጽኦ በአደባባይ በማሳየት ሀገርና ሕዝብን መለወጥ እንደሚገባው ተናሯል። ኪነ ጥበቡን በመጠቀም የኢትዮጵያዊነት አንድነት ማጉላት እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ገጣሚና ተዋናይነት የዱርፍሬ ይፈሩም የሀገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል ። የኪነ ጥበብ ባለሙያዋ እንዳሉት ኢትዮጵያ እናት ናት ስለሆነም ሁሉም እናቱን ሊሰማ ይገባል። እናቱን የሚያስቀይም ሥራ ማንም መሥራት እንደሌለበትም መክረዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ረጅም ዕድሜ ያላት እናት ናት ‹በዛችሁብኝ ተበታተኑ› አላለችምና ሁሉም መልካም እናቱን ማስከፋት አይገባውም›› ብለዋል ገጣሚዋና ተዋናይ የዱርፍሬ።

‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ሲባሉ ለውጭ ጠላቶች ዕድል መስጠት ስለሚሆን ሁሉም በእናቱ ጉያ በአንድነት መኖር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ይህ ትውልድ ክፉ ቀንን አላዬም፤ በሠላም ሀገር በሠላም አየር ነው የተወለደው፡፡ ክፉ ቀን የሚያውቁት አባቶቻችን ናቸው። ያ ክፉ ቀን ሲመጣ የቱን ጥዬ የቱን አጥንልጥዬ ይመጣል። ያ እንዳይመጣ ኢትዮጵያን ያስጨነቃትን ነገር በጋራ መፍታት አለብን›› ሲሉም አስጠንቅቀዋል ።

‹‹የኢትዮጵያ አንድነት መናጋት ብዙ አልራቀም›› ያሉት የኪነ ጥበብ ባለሙየዋ የኪነ ጥብ ባለሙያው የጎበጠውን ማቃነት እንዳለበትም አሳስበዋል ። ክፉ ቀን ከምምጣቱ በፊት ክፉን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የመጀመሪያው አማራና ኪነ ጥበብ ውይይት ዓለማው ከአማራ ክልል የፈለቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እርስ በርስ ተቀራርበው ሙያቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠርና በየአቅጣጫው እየተጎነተለ ላለው የክልሉ ሕዝብ አንድነት ላይ በመሥራት ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ እንደትሄድ ለማስቻል ነው። በመድረኩ የክልሉን ርዕሰ መስተደድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የክልሉ የሠላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ጀማሪ የኪነ ጥብብ ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ምክክሩ ዛሬና ነገ የሚቀጥል ነው፡፡

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

Previous articleየአማራ ክልል ሰርከስ ማኅበር በባሕር ዳር ተመሠረተ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ ከአንድ ላም በአማካይ የሚገኘውን 1 ነጥብ 8 ሊትር ወተት ወደ 30 ሊትር ለማሳደግ እየተሰራ ነው።