
ከሚሴ:መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተያዘው የ2015 ዓ.ም የመስኖ ወቅት በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በ1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው። 1 ሺህ 200 ሄክታሩ የስንዴ ሰብል በክላስተር የተዘራ ስለመኾኑም የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የዕቅድ እና ክትትል ባለሙያ አቶ ሙክታር አወሉ ተናግረዋል።
የበጋ ስንዴ ልማቱ “ሰላማችን በመጠበቅ ልማታችን እናስቀጥላለን” በሚል ንቅናቄ እየተካሄደ እንደሚገኝም አቶ ሙክታር ነግረውናል። የሕልውና መሠረት ለሆነው ግብርና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወረዳው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ባለሙያው ተናግረዋል።
አቶ ሙክታር እንደገለጹት በወረዳው በ2015 ዓ.ም 1 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ተሸፍኗል። ይህም ባልጭ፣ ወሰን ቁርቁር፣ ጥቁሬ፣ መሩዋ እና ሌሎች የመስኖ ተጠቃሚ አከባቢዎች ላይ የለማ ነው። ወረዳው በጦርነት ምክንያት በደረሰው ውድመት ምክንያት በፈተናዎች ውስጥ ቢኾንም የበጋ ስንዴ ልማትን በቁርጠኝነት ይዞ እየሠራበት እንደሚገኝ አቶ ሙክታር ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!