
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሀብት ልማት ፕሮጀክት ለመጀመር የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶክተር ኢንጂነር) ፣ የአማር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት አስራት አጸደወይን (ዶክተር) ፈርመውታል። በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሃብት ልማት ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የወተትና የስጋ ምርትና አቅርቦት በማሳደግ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማሳደግ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የኢትዮጵያ ላሞች አማካይ የወተት ምርት በአንድ ላም በቀን 1 ነጥብ 8 ሊትር እንደሆነ በስምምነቱ ላይ ተገልጧል፡፡ በቴክኖሎጂ በመደገፍ አሁን እየተገኘ ያለውን ዝቅተኛ የወተት ምርት በቀን ወደ 30 ሊትር ለማሳደግ እቅድ እንደተያዘ ነው የተገለጸው። ይህም አሁን እየተገኘ ካለው በ28 ነጥብ 2 ሊትር የሚበልጥ የወተት ምርት ለማግኘት ያስችላል፡፡
ፕሮጀክቱ የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል፣ ለስጋና ለወተት ምርት የሚሆን መኖ ማዘጋጀት፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት አረባብ እና የገበያ ትስስርን እንደሚያካትትም ታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ሀሳቡን ተግባራዊ ለማድረግም ስምምነት ተፈርሟል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሀብት ልማት ፕሮጀክት በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ምንጭ፡- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር