“በዞኑ ከ12 ሺህ 300 በላይ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሲሰሩ በመገኘታቸው ርምጃ ተወስዷል” የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ

61
ደብረ ብርሐን:መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በበጀት ዓመቱ የኑሮ ውድነቱን በማባባስ በሕገወጥ መንገድ ሲነግዱ የተገኙ ከ12 ሺህ 300 በላይ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ ሕግ የማስከበር ርምጃዎች መውሰዱን ገለጸ ፡፡
መምሪያው አሁን ባለው የምርቶች የገበያ ዋጋ መጨመርና የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተክለየስ በለጠ እንደገለጹት ፤ በዞኑ ማኅበረሰቡን ከኑሮ ውድነቱ ለማገዝ በበጀት ዓመቱ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በቀጥታ ከአምራቹ ምርት ገዝተው ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ በተደረገው አሰራር መሰረት 30 ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች እስከ 5 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት ይዘው እየተሰራበት ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት እንደ ዞን 67 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በጀት ተይዞ ዋና ዋና የፍጆታ ምርቶች በማቅረብ ኅብረተሰቡን ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
አሁን ካለው የፍጆታ ምርቶች የዋጋ ንረት አኳያ የተያዘው በጀት በቂ ባይሆንም አንዳንድ ወረዳዎች ዋና ዋና የፍጆታ ምርቶችን በማቅረብ ማኅበረሰቡን በማገዝ እንዲሁም ለመንግሥት ሰራተኛች በ3 ወር ክፍያ ጤፍና የዳቦ ዱቁት በማቅረብ በኩል ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የኑሮ ውድነቱን ከመቆጣጠር አኳያ አንዳንድ ወረዳዎች የተሻለ ሥራ እየሰሩ የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ ግን ለሕዝቡ ችግር እየደረሱ አይደለም ብለዋል።
ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ቢኖሩም ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ምርት ገዝተው እንዲያቀርቡ በተቀመጠላቸው መመሪያ መሰረት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
ሕግን ከማስከበር አኳያ በበጀት ዓመቱ 12ሺ 322 ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሲሰሩ ተገኝተው ርምጃ ተወስዷል ያሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የ1ሺህ 991 ነጋዴዎች የንግድ ቦታዎችን ማሸግ፣ 7ሺህ 998 የሚሆኑትን ከሥራ ማገድና 6 ነጋዴዎች ላይም ክስ ተመስርቷል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሕገወጥ መሰረታዊ ምርቶችን በመያዝ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በታየው የግብርና ምርቶች ዋጋ መጨመር በተደረጉ አሰሳዎች በዞኑ በሕገወጥ ንግድ ሲሰሩ የተገኙ የ446 ነጋዴዎች የእህል ንግድ ቤቶች ታሽገዋል፤ እንዲሁም 96 የሚሆኑትን አግደናል ያሉ ሲሆን ይህ ገበያ ውስጥ ካለው ሕገወጥ ነጋዴ ብዛት አኳያ ርምጃው አናሳ መሆኑን ነው ያነሱት ።
አሁን ላይ ያለውን የገበያ ቀውስ አስመልክቶ ሰሞኑን በክልልና ዞን በተደረጉ የምክክር መድረኮች ሕገወጥና ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ በንግድ ተቋማትና ማዕከላት ላይ በዘመቻ ቁጥጥር እንዲደረግ ተወስኖ በየወረዳዎች ወደ ሥራ ተገብቷል ።
በዞኑ ከሚጠቀሱት ችግሮች ውስጥ የሕገወጥ ነጋዴዎች በግብይት ሥርዓት ውስጥ በመግባት በአምራቹና በነጋዴው ውስጥ እየገቡ የሚሰሩ ደላሎች መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው፤ ሌላው ነጋዴዎች ካስመዘገቡት ካፒታል በላይ በሆነ ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ እየሰሩ መገኘታቸውም አንዱ ፈተና መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በሌላ በኩል የዘይት ምርቶችን ወደ ዞኑ ለማጓጓዝ በጸጥታ ስጋቶች ምክንያት እስካሁን ማቅረብ አለመቻሉንም አንስተዋል፡፡
ነጋዴው አብሮት የሚኖረውን ሕዝብ በኑሮ ውድነት ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን ተረድቶ ተመጣጣኝ ትርፍ እያገኘ ኅብረተሰቡን በማገዝ እንዲተባበር በማለት ኃላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል። የዘገበው የሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከስፖርቱ ዓለም ታሪክ በዚህ ሳምንት!
Next article“በዞኑ ከ12 ሺህ 300 በላይ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሲሰሩ በመገኘታቸው ርምጃ ተወስዷል” የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ