
ባሕር ዳር:መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደከመን የሚያሳርፉት፣ የተራበን የሚያጎርሱት፣ የተጠማን የሚያጠጡት፣ የታረዘን የሚያለብሱት፣ የተከፋን የሚያጽናኑት፣ የተቅበዘበዘን የሚያረጋጉት የታመመን የሚጠይቁት፣ ጥላ ላጣ ጥላና ከለላ የሚሆኑት፣ ሰውን ከራስ በላይ የሚወዱት ደጋጎቹ ቤት ናፈቃቸው፣ ቀዮው ውል አላቸው፤ ጋራና ተራራው፣ ሸንተረርና ሜዳው በዓይናቸው ዞረባቸው፡፡
ወደ ምንጭ ወርደው የሚቦርቁት፣ ቀዬውን እያካለሉ የሚደሰቱት፣ በአንድነት የሚጫወቱት፣ በደስታና በፍቅር የሚኖሩት ልጆች ቀያቸውን አብዝተው ናፈቁት፡፡ ዋሽንት እየተጫወቱ በዜማ ለልብ ሃሴትን የሚሰጡት፣ ጋራና ጋራ ላይ ሆነው ግጥም የሚቀባበሉት እረኞች ተወልደው ያደጉበትን፣ ደስታና ፍቅር ያዩበትን፣ ጠዋትና ማታ የተመላለሱበትን፣ በሠርጉና በማኅበሩ የተገናኙበትን፣ በአበው እየተመረቁ የኖሩበት ቀዬ ርቋቸዋልና ከፋቸው፡፡ ወተት የማይታጣበት፣ ፍቅር የመላባት ቀዬ ዛሬ ላይ እየኖሩባት እየተደሰቱባት አይደለችምና አብዝቶ አሳዘናቸው፡፡ በረኃ ወርደው ከላሞቻቸው እና ከፍየሎቻቸው የሚጠጡት ወተት አምሯቸዋል፡፡
ዛሬ ላይ የፍየል መንጋ በማያዩበት፣ወተት በማይታለብበት፣ እንደ አሻ መቦረቅ በማይቻልበት፣ ዋሽንትም በማይጫወቱበት ፣ በጋራው ወጥተው በማያዜሙበት ውስጥ እየኖሩ ነውና ልባቸውን ሀዘን ገባው፤ ዓይናቸውን እንባ መላው፣ ጎንጫቸውን የእንባ ዘለላ ተመላለሰበት፡፡
መቀመጥ የማይወዱት፣ ማሳቸውን ሳያዩ የማይውሉት፣ ከበሬዎቻቸው እሸት ፣ ከላሞቻቸው ወተት የማያጡት ደጋግ ገበሬዎች እጅ አግራቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው ዋሉ፡፡ ለሰዓታት መቀመጥ የማይወዱት፣ ለቀናት፣ ለሳምንታት፣ ለወራት እያለ ቀጠለባቸው፡፡ በሞቀ ቤታቸው ልጆቻቸውን ያኖሩት እናቶች የልጆቻቸውን ፊት የሰው ዓይን ገረፈባቸው፣ እናቴ እራበኝ ሲሏቸው የሚሰጡት ጠፋባቸው፣ የልጆቻቸውን መከፋት አይተው ሀዘን ገባቸው፡፡

በማኅበሩ፣ በዝክሩ፣ በሰርጉ የሚገናኙት፣ በደስታና በዓለም የኖሩት እኒያ ደጋጎች ቤት እያላቸው ቤት ናፈቃቸው፡፡ እንግዳ የሚቀበሉት፣ የመሸበትን የሚያሳድሩት፣ አብልተው አጠጥተው ስንቅ አስይዘው የሚሸኙት ልበ ቀናዎች መመላለሻው ራቀባቸው፣ አርሰው የሚጎርሱበት፣ አልበው የሚጠጡበት ጊዜ ረዘመባቸው፡፡ እንኳን እርቀዋት እየኖሩባት የማይጠግቧትን ቀያቸውን፣ ገመና ሸካፊ ቤታቸውን ናፈቋት፣ በአሻገር ሆነው ሳሱላት፡፡ ከማብላትና ከማጠጣት ውጭ ክፋት ያልተገኘባቸው እናቶች፣ አርሶ ከማፈስ በስተቀር በደል ያልተቆጠረባቸው አባቶች፣ ቤትና ንብረታቸውን ጥለው ልጆቻቸውን አስከትለው ተንከራተቱ፣ ራባቸው ጠማቸው፡፡ ዘመን አስከፋቸው፣ ጊዜ ገፋቸው፤ ሰሚና አስታዋሽ ራቀባቸው፡፡
በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚጣሩ አንደበቶች፣ አጉራሽ ያጡ ጎሮሮዎች ሞልተዋል፡፡ ሰላም ሲሆን ቀያችን ይለቀቃል ያሉ ባለ ተስፋዎች አሁንም በመጠለያ ውስጥ በሀዘን ተቀምጠዋል፡፡ ቀያቸውን ናፍቀዋል፡፡ በሕወሃት ታጣቂዎች በተያዙ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ዛሬም የመከራ ጊዜን እየገፉ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ አፈናውን እና መከራውን ሽሽት ቀያቸውን ለቀው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ኖሯቸውን ቢያደርጉም የመጠለያ ሕይወት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፡፡
ደባሽ ገብረእግዚ ይባላሉ፡፡ ትዳር ይዘው፣ ልጆች ወልደው የኖሩበት አበርገሌ ነው፡፡ አባውራው ስምንት ቤተሰቦች አሏቸው፡፡ አሁን ላይ ‘በጥርቂ’ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ መኖሪያቸውን አድርገዋል፡፡ በወረራው ምክንያት ቀያቸውን ከለቀቁ ቆይተዋል፡፡ ʺሚሰቴን ልጆቼን ይዤ ቤቴን ዘግቼ ነው የተቀመጥኩት፡፡ ስምንት ቤተሰቦቼን ይዤ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እኖራለሁ፡፡ ድጋፎች አሉ፡፡ ነገር ግን ጊዜውን አይጠብቁም፣ የሚሰጠውም በቂ አይደለም፡፡ በቤታችን እያለን እርሻም እያረስን፣ ንግድም እየነገድን አሥራ አምስት ኪሎ እንደገፍ ነበር፤ ይህም ከምንሠራው ጋር ሲጨመር ጥሩ ነበር፡፡ አሁን ግን መነገድም ማረስም አንችልም፤ አሥራ አምስት ኪሎ ግራም መጥታ ከምንም አትደርስም” ነው ያሉኝ፡፡
ምግብ የሚሉ ልጆችን ይዘው ከዓመት በላይ በመጠለያ ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ችግሩን እና ጉስቁልናውን ችለው ቀያቸውን እያሰቡ ይኖራሉ፡፡ አሁን ላይ የውኃ እጥረት እንዳለባቸውም ነግረውኛል፡፡ በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችም ምንጭ ፍለጋ ይጓዛሉ፡፡ ድንገተኛ የሚባለው እርዳታ እንደቆመባቸውም ነግረውኛል፡፡ አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ቀደም ሲል የነበረው መደበኛ ድጋፍ ነው፡፡
ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ የነገሩኝ አባወራው ደባሽ “ትመለሳላችሁ ካሉን ቆይተናል፣ ነገር ግን የሚነግሩን አልሆነም፤ አንድ ክረምት አልፎናል አሁንም ካለፈው ችግራችን እየከፋ ነው የሚሄደው” ብለውኛል፡፡
ሌላኛዋ ‘በጥርቂ’ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩት የስድስት ቤተሰቦች እማውራ ሽዋዬ ቢፈርደው ናቸው፡፡ ሽዋዬ ከመኖሪያ ቀያቸው ጻግብጂ ከወጡ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ለሁለት ዓመታት ልጆች ይዞ መንከራተት ሕይወታቸውን እንዳከበደባቸው ነግረውኛል፡፡ ከቀያቸው ሲወጡ ሃብትና ንብረታቸውን ተወርሰው ባዶ እጃቸውን እንደወጡም አስታውሰዋል፡፡
ሸዋዬ የሞቀ ቤታቸውን ከለቀቁ በኋላ ወልደዋል፡፡ ከባድ የአራስነት ጊዜንም አሳልፈዋል፡፡ የጎረቤት ጥየቃው፣ ለአራስ የሚደረገው እንክብካቤ እና ጥበቃ ለሽዋዬ ከቤታቸው ጋር በጻግብጂ ቀርቷል፡፡ ያ የአራስነት ጊዜ ትዝታ ብቻ ሆኗል፡፡ እሳቸው ልጃቸውን በችግር ውስጥ ሆነው ወለዱ፡፡ የሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑንም ነግረውኛል፡፡ ረጅ ድርጅቶች አሁን ላይ ቀርተዋልም ብለዋል፡፡
ዓለማየሁ በርሄ ደግሞ ቀያቸውን ከለቀቁ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ከመስከረም ወዲህ ድጋፍ ቀንሷል፣ ተቸግረን ነው የምንኖረው ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ አስቸጋሪ ሕይወት እንደሚመሩም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ቀያቸውን ሰላም አድርጎ እንዲመልሰን እንሻለንም ብለዋል፡፡ ባዶ መሬት ላይ እንደሚተኙም ነግረውኛል፡፡ ʺየምንፈልገው ወደ ቤታችን መመለስ ነው፣ ወደ ቤታችን ከተመለስን በኋላ ቤታችን የምንሠራበትና የምንቋቋምበት ድጋፍ እንፈልጋለን” ነው ያሉኝ፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ቡድን መሪ ዝናሽ ወርቁ በአራት መጠለያ ጣቢያዎች ሕይወታቸው እየገፉ የሚገኙ ወገኖች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ67 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ተፈናቅለው በመጠለያ እና በዘመድ አዝማድ ቤት እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡
እየተሰጣቸው ያለው ድጋፍ መደበኛው እንጂ ድንገተኛ ድጋፍ መቆሙንም ተናግረዋል፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በባለሃብቶች ሲደረግ የነበረው ድጋፍ አሁን ላይ መቆሙንም አስታውቀዋል፡፡ አሁን እየተሰጣቸው ያለውን ድጋፍ በቤታቸው ሆነውም ሊያገኙት የሚችሉት መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ ወደ ቀያቸው መመለስ ካልተቻለ ችግሮቻቸውን መፍታት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን አስፈጽሞ ወደ ቀያቸው ሊመልሳቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ድንገተኛ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች አሁን ላይ ባለመኖራቸው ኢትዮጵያውያን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን እንዲደግፉም ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ መስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ታየ ጌታቸው ረጅ ድርጅቶች እና መንግሥት ቦታ ተከፋፍለው ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ረጅ ድርጅቶች ከመንግሥት በተሻለ ድጋፍ እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል፡፡ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባልተለቀቁ ወረዳዎች ላይም በቂ ባይሆንም ድጋፍ እያደረሱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አመልድ እና ሌሎች ተቋማት በሥፍራው ድጋፍ ያደርጋሉም ብለዋል፡፡
እጥረቶች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ ተፈናቃይ ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ አያገኙም ማለት ግን አይደለም ብለዋል፡፡ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖችም ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ የአማራ ክልል ምክር ቤት ባደረገው ጉባዔ የአማራ ክልል መንግሥት ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡ ወደ ቀያቸው ለመመለስም እየሠራ መሆኙን አስታውቋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!