
ባሕርዳር: መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ በ16 ጥሎ ማለፍ ከሪያል ማድሪድ ጋር የተገናኘው ሊቨርፑል በደርሶ መልስ ጨዋታ ተሸንፎ ተሰናብቷል።
ሊቨርፑል በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳው አንፊልድ 5 ለ 2 መሸነፉ ይታወሳል።ወደ ነጮቹ ቤት ቤርናባው አቅንቶ ውጤቱን ቀልብሶ ለማለፍ እንደሚጫወት ሲጠበቅ በቤርናባውም 1ለ 0 ተሸንፏል። የሪያል ማድሪድን የማሸነፊያ ግብ አጥቂው ካሪም ቤንዚማ አስቆጥሯል።
የመድረኩ ንጉሥ ሪያል ማድሪድ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል። ማድሪድ ዘንድሮም ለዋንጫው ሁነኛ ተፎካካሪ እንደሚኾን ይጠበቃል። በሌላ ጨዋታ የጣልያን ሴርኤ መሪው ናፖሊም ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል። በሜዳው የጀርመኑን ኢንተራ ፍራንክፈርትን ያስተናገደው ናፖሊ 3 ለ 0 በማሸነፍ ነው ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለው።
ናፖሊ 3 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ናይጀሪያው አጥቂ ቪክቶር ኦስማህን ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ቀሪዋን ግብ ዘለንስኪ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።

በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜውን ከተቀላቀሉት ስምንት ክለቦች መካከል ሦስቱ የጣልያን ክለቦች ናቸው። ናፖሊ፣ ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ የጣልያን ክለቦች ሆነዋል።
ማንችስተር ሲቲና ቸልሲ ከእንግሊዝ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው። ሪያል ማድሪድ ከስፔን፣ ባየርን ሙኒክ ከጀርመን እና ቤኔፊካ ከፖርቹጋል ናቸው ሌሎች ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች።
በአውሮፓ ከአምስቱ ታላላቅ ሊጎች አንዱ የኾነው የፈረንሳይ ሊግ አንድ አንድም ቡድን ለሩብ ፍጻሜው አላሳለፈም። የዓለም የእግር ኳስ ከዋክብትን የሰበሰበው ፒኤስጂ በጊዜ መሰናበቱ ይታወሳል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!