“በኅልውና ዘመቻው ትክክለኛውን የሙያ ሥነ ምግባርና ተግባር በእናንተ ውስጥ አይተናልና ልትመሰገኑ ይገባል” የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ

234
ሁመራ፡ መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኅልውና ዘመቻው በሙያቸው በመዝመት ለወገን ጦር አባላት የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ለተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና መርኃ ግብር በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩም የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ጠቅላይ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችና የዞን አሥተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር አየለ ተሾመ፤ የሕክምና መስጫ ግብዓት ባልተሟላበት ዞን ውስጥ ኾናችሁ ትክክለኛውን የሙያ ሥነ ምግባርና ተግባር በእናንተ ውስጥ አይተናልና ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም በተሠማራበት ሙያ ለሀገሩ በመዝመት የሀገርን ሉዓላዊት ማስቀጠል መቻሉ በታሪክ የሚታወስ መኾኑንም ተናግረዋል።
በኅልውና ዘመቻው በዞኑ በተለያዩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ሲያገለግሉ የነበሩ ከ200 በላይ ባለሙያዎች ወደ ግንባር በመዝመት በሙያቸው አገልግሎት መስጠታቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ አቶ መንገሻ ንጉሱ ገልጸዋል። ባለሙያዎች በሙያቸው ያሳዩት ተጋድሎ የሚደነቅ መኾኑንም አንስተዋል።
May be an image of 3 people, people standing and indoor
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ሀገር ፈተና ላይ በወደቀችበት ወቅት የዞኑ የጤና ባለሙያዎች ከሌሎች የሀገራችን ባለሙያዎች ጋር በመኾን የሠራችሁት ሥራ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
የተሰጣችሁ እውቅና በቀጣይ ለማኅበረሰቡ የተሳለጠ የሕክምና አገልግሎት እንድትሰጡ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ያሉት ዶክተር መልካሙ ባለሙያዎች በትኩረትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው፤ በዞኑ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሳይከፈላችሁ ለ24 ስዓት በሙያችሁ ለሀገራችሁ አገልግሎት በመስጠታችሁ ለሌሎች ባለሙያዎች ተምሳሌት በመኾናችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።
በተሰጣቸው እውቅና ደስተኛ መኾናቸውን የተናገሩት ዘማች የጤና ባለሙያዎች የተሰጣቸው እውቅና በቀጣይ ኅብረተሰቡን በትጋት ለማገልገል መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ያየህ ፈንቴ
                 ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከግጭት ጋር ተያይዞ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ሊተባበር ይገባል” ጤና ሚኒስቴር
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ.ብሊንከን ጋር ተወያዩ።