
ባሕር ዳር:መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት መጠነ ሰፊ ውድመት እና መፈናቀል ደርሷል። ይህንን ውድመት በተደራጀ መልኩ መልሶ ለመገንባት ሥራውን በባለቤትነት የሚመራ ተቋም በማስፈለጉ የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጥር/2014 ዓ.ም ተቋቁሟል። የፈንድ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) ከአሚኮ ኦንላይን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ዶክተር አባተ እንዳሉት ሐምሌ1/2014 ዓ.ም ላይ ሥራውን በይፋ የጀመረው የፈንድ ጽሕፈት ቤቱ ተቀዳሚ ተግባር የደረሰውን ውድመት አንድ በአንድ በጥናት መለየት ነበር።
ከአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር በመተባበር 4 ሺህ 500 ምሁራን የተሳተፉበት ጥናት መካሄዱንም ተናግረዋል። ጥናቱ ጦርነቱ የነበረባቸውን የክልሉ 7 ዞኖች፣ 87 ወረዳዎች እና 945 ቀበሌዎች ያካተተ መኾኑንም ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ብቻ 292 ቢሊዮን ብር የሚገመት ቁሳዊ ሃብት መውደሙ በጥናቱ ተረጋግጧል። የደረሱ ሰብዓዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳቶችም ቤት ለቤት ተለይተው ተጠንተዋል።
የደረሱ ጉዳቶች በሙሉ በመጽሐፍ ተሰንደው እና ዓለም አቀፍ ዌብ ሳይት ጭምር ተከፍቶ ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ውድመቱ መጠነ ሰፊ ቢኾንም ወደ ተግባራዊ የመልሶ መቋቋም እንቅስቃሴ ለመግባት በዚህ ዓመት የተመደበው በጀት አንድ ቢሊየን ብር ብቻ ነው። እስከአሁን 11 ክሊኒኮች፣ 22 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ አስር ለወጣቶች ሥራ ዕድል የሚፈጥር ማዕከል መሠራቱን የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ:-





በተበጀተው 1 ቢሊዮን ብር በዓመቱ የተጀመሩ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እስከ ግንቦት/2015 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ ተብሏል።
አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ምንም አይነት የመልሶ ማቋቋም ግንባታ እንዳልተጀመረ ለዋና ሥራ አስኪያጁ ጥያቄ አቅርበን ነበር። የወረዳዎች የውድመት መጠን የተለያየ በመኾኑ ለባሰው አካባቢ ቅድሚያ እየተሰጠ የመልሶ ማቋቋም ሥራው በሁሉም ወረዳዎች በቅደም ተከተል እና በፍትሐዊነት ተደራሽ እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ በተሰጠው የአምስት ዓመት የቆይታ ጊዜ ውስጥ በሁሉም አካባቢ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ዶክተር አባተ በክልሉ ላይ የደረሱ ሁሉንም ውድመቶች መልሶ ለመገንባት እና ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም 475 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በጥናት ተለይቷል ብለዋል። ከውድመቱ አንጻር የተበጀተው 1 ቢሊዮን ብር በቂ አይደለም። ከዚህ በጀት በተጨማሪ በሴክተር መስሪያ ቤቶች በኩል ለመልሶ ማቋቋም ሥራው እስካሁን ድረስ 10 ቢሊዮን ብር ወጭ መደረጉንም ዶክተር አባተ ተናግረዋል።
ዶክተር አባተ የፌደራሉ መንግሥት ለፈንድ ጽሕፈት ቤቱ ትኩረት መስጠት ባለበት ልክ ትኩረት እንዳልሰጠው ተናግረዋል። የደረሰውን መጠነ ሰፊ ውድመት መልሶ ለማቋቋም በክልሉ በጀት ብቻ የማይቻል መኾኑ ታውቆ የፌደራል መንግሥት በትኩረት ይዞ ሊሠራበት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ በአማራ ክልል ከ1 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ወደየቀያቸው እስከሚመለሱ ድረስ ሰብአዊ ድጋፍ ከማቅረብ ጀምሮ በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም በጋራ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል። ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች ወደክልሉ ገብተው እርዳታ እንዲያደርጉ የተቀናጀ ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛል። እስካሁን ሁለት ብቻ ረጅ ድርጅቶች እንደገቡ እና ሌሎችም በቅርብ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ዶክተር አባተ ገልጸውልናል።
ዶክተር አባተ “አሁን ያለውን ፈተና ለመወጣት ልዩ ጥንካሬ ያስፈልጋል” ሲሉ ገልጸዋል። የችግሩ ሰለባ የኾኑ ዜጎች ከሚደረግላቸው እርዳታ በተጨማሪ የራሳቸውን ልዩ ጥንካሬ እና ጥረት ተጠቅመው ይህንን ጊዜ ማለፍ ይገባል ብለዋል። እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ ተንቀሳቅሰው በመሥራት ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከችግር ያወጡ እንዳሉም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ላይ የደረሰው ውድመት እና መፈናቀል መጠነ ሰፊ ቢኾንም በመተባበር እና በልዩ ብርታት ከችግሩ ለመውጣት መረባረብ ያስፈልጋል። ዶክተር አባተ “በአማራ ክልል ያለውን መጠነ ሰፊ ውድመት እና ችግር አሽቀንጥሮ በመጣል ነገን የተሻለ ለማድረግ አንድነት፣ ልዩ ብርታት እና ተደጋግፎ መሻገር ግድ ይላል” ብለዋል። በተለይም ተጎጅዎች ከችግር ለመውጣት ልዩ ብርታት መላበስ እንዳለባቸውም ዶክተር አባተ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጦርነት ጉዳት ያልደረሰባቸው የክልሉ አካባቢዎች ተጎጅ የኾኖ እህትና ወንድሞቻቸውን ማስታወስ እና ወደየቀያቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል። የረጅ ድርጅቶችን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ የእርስ በእርስ መደጋገፍ ባሕልን ማጎልበት ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ እንደሚኾንም ዶክተር አባተ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!