
የአማራ ክልል ሕዝብ ለኪነ ጥበብ ካበረከተው አስተዋጽኦ አንጻር ከዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
‹‹አማራና ኪነ ጥበብ›› በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር የኪነ ጥበብ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ‹‹የኪነ ጥብና የስነ ጥበብ ባለሙያዎችን አምጦ እየወለደ፣ ተንከባክቦና ሙያቸውን አክብሮ እያሳደገ ለቁም ነገር ካበቃ በኋላ መጠቀም ሲችል ሙያውን የሚያከብረውን ያህል፣ ለሙያው ባለው አክብሮትና ግንዛቤ ልክ አምጦ የወለዳቸውንና በዓለም አደባባይ ዕንቁ የተሰኙ ሙያተኞቹን ሳይጠቀም የቆዬ ሕዝብና ክልል ነው›› ብለዋል፡፡
የዛሬው ጉባኤ ዓላማም ሙያተኞቹን ለሠላም፣ ለልማት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለማኅበራዊ ዘርፍ ዕድገት ለመጠቀም እንደ መነሻ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው አመላክተዋል፡፡
የአማራ ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ሙያተኞች አገራቸውን ከሁሉም አስቀድመው በመሥራታቸው የሀገሪቱ ትናንት፣ ዛሬና ነገ አስመልክተው በየጊዜው የሚነሱ አበርክቶቶች እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተዝቆ በማያልቅ ቱባ ባሕላቸው ‹እኔ፣ ብሔሬ፣ ወንዜ› ሳይሆን ‹ሀገሬ› በማለት ‹እኔን ያስቀድመኝ› የሚሉና ይህም ለትውልድ የተላለፈና ዛሬም ያለ ነው›› ብለዋል፡፡
አሁን እንደ ሀገር ከተገባበት ቀውስ ለመውጣት የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎቹ የተለመደ ረቂቅ ፈጠራቸውን እንዲጠቀሙም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡ ከቀደምት አያት ቅድመ አያት በቅብብሎሽ ከዚህ የደረሰችውን ኢትዮጵያ ለቀጣይ ትውልድ እስከ ክብሯ ለማድረስ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎቹ መስመር እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ እስከ ዳግማዊ ምኒልክ የቤተ መንግሥቱ እንቅስቃሴ ኃያሲ የነበሩትን አለቃ ገብረሐናን ጨምሮ ተዋናይ ዘጎንጂን፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን፣ እመይቴ ገላነሽን፣ አራት ዐይና ጎሹንና ሌሎችንም በምሳሌነት ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተጠቀሱት ሊቃውንት የዘመኑ የኪነ ጥብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎችም በሐሳብ እንዲመሩ ነው ያሳሰቡት፡፡
በተዛባ ትርክት የአማራ ሕዝብ ዋጋ እንዲከፍል ያደረጉ ከስህተታቸው መታረም እንዳለባቸውና በሕግ መጠየቅ የሚገባቸውም በሕግ እንዲጠየቁም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹እኛ ከአባቶቻችን ተሽለን መገኘት ይገባን ነበር፤ አባቶቻችን የእርስ በእርስ መተማመንና በጋራ ለልማትም ይሁን ለጦርነት የመሠለፍ ብቃት ነበራቸው፡፡ ለሁሉም ነገር አይቸኩሉም፤ ቁጥብና ርጋታን የተካኑ ነበሩ›› ያሉት አቶ ተመሥገን ልዩነቶችን በመቻቻልና በውይይት የመፍታት የዳበረ ልምድ እንደነበራቸውና ይህንን መውረስ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡