በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ክልሉ ፈጥኖ ማቋቋም እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ አሳሰቡ፡፡

435

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሰሞኑ በተቀሰቀሰው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በአፋጣኝ መልሶ እንዲያቋቁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ጠየቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹የፀጥታ ኃይል ባለበትና በፖለቲካ ልዩነት ንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሚወገዝ ነው›› ብለዋል።
አቶ ተመሥገን ለኢዜአ እንደተናገሩት የአማራ ሕዝብ ከክልሉ ውጭ በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ከሁሉም ጋር በጋራ መኖር የሚችልና የዜጎችን በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራት የሚደግፍ ነው።
ያም ሆኖ በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች የብሔርና የሃይማኖት መልክ የሚይዙ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ንጹሐን ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።
‹‹ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭትም ተዋልዶና ተሳስሮ የሚኖር ሕዝብ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በመጻረር በንጹሐን ላይ የደረሰውን ጥቃት የክልሉ መንግሥት ያወግዘዋል›› ብለዋል።
ወደ አገር ልማት የሚገባው ቅድሚያ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሲቻል መሆኑን ገልጸው መንግሥት ሕግ የማስከበር አቅሙን መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።
በግጭቱ ሁሉም ሕዝብ ተጎጂ መሆኑን ገልጸው በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት መድረስ እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግሥት ከሰሞኑ በደረሰው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በአፋጣኝ ማቋቋም እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም ለሚደረገው ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ
Next articleየአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡