“በአማራ ክልል 757 ሺህ ወገኖችን ከዓይነ ሥውርነት መታደግ ተችሏል” የክልሉ ጤና ቢሮ

133

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በትራኮማ በሽታ ምክንያት የዓይን ቆብ ፀጉር መቀልበስ ችግር ተጠቂ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መድረክ በባሕርዳር እየተካሄደ ነው። በአማራ ክልል አሁንም ድረስ የትራኮማ በሽታ በስፋት እንዳለ ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በክልሉ የትራኮማ በሽታን መከላከል እና መቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል። ነገር ግን በክልሉ አሁንም ከፍተኛ የኾነ የተራኮማ በሽታ መኖሩን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል 130 ሺህ ወገኖች የዓይን ፀጉር መቀለብስ ችግር አለበቸው ብለዋል። ከእነዚህ መከካል እስካሁን የተሠራው 20 ሺህ የሚሆኑትን ነው። ቀሪ ወገኖችን ከዓይን ፀጉር መቀልበስ ለመታደግ በርብርብ መሥራት እንደሚገባም ገልፀዋል። የዓይን ፀጉር መቀልበስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዘመቻ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶችን ማስፋፋት የተራኮማ በሽታን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የትራኮማ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተደረገው ሥራ በክልሉ 757 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ከዓይነ ሥውርነት መታደግ ተችሏል ነው ያሉት።

ሕዝቡን በማሳተፍ በንቅናቄ በመሥራት ችግሮችን መፍታት አለብንም ብለዋል። የዓይን ጭራ መቀልበስ ላይ ሕክምና ሊሠጡ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማስልጠናቸውንም ገልዋል። የሰለጠኑ ባለሙያዎች ግን በሚገባው ልክ እንዲሠሩ አለመደረጋቸውን ተናግረዋል። የዓይን ጭራ መቀልበስን ለመከላከል ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎች እና እስከታች ያለው መዋቅር ሕዝቡን በማሳተፍ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከ200 በላይ ለመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ፈላጊዎች ማኅበራት የብሎክ እጣ መርሃ ግብር አካሄደ።
Next article“በንግግር ብቻ የሚፈታ ችግር የለም፣ ችግር የሚፈታው በተግባር ነው” በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን