
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ፈላጊዎች ማኅበራት በተለያየ ጊዜ የቤት መገንቢያ ቦታ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል። ዛሬም ከተማ አሥተዳደሩ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ሲደራጁ የቆዩ በአጠቃላይ 5 ሺህ 67 አባላትን ያቀፉ 229 ማኅበራት የብሎክ እጣ መርሃ ግብር አካሂደዋል።




229 ማኅበራት ናቸው የብሎክ እጣን ያወጡት።
የብሎክ እጣ ካወጡት ማኅበራት አባል መካከል ይርጋ ግዛቸው እንዳሉት ማንኛውንም የተጠየቁትን መስፈርት ቢያሟሉም ከመመሪያው ውጭ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄያቸው ሳይመለስ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከረጅም እንግልት በኋላም ቢኾን ጥያቄያቸው የተመለሰ በመኾኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ሌላው የብሎክ እጣ ያወጡት መምህር አምድይሁን ጓሉ የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ባለመኖራቸው ሕይዎታቸውን በቤት ኪራይ እያሳለፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። “በተለይ በአሁኑ ወቅት ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ የቤት ኪራይ በመጨመሩ የስቃይ ኑሮ ነው እያሳለፍን የምንገኘው” ያሉት ነዋሪው መንግሥት ለቀሪ የመኖሪያ ቤት ቦታ ፈላጊዎች መልስ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። መምህር አምድይሁን እንዳሉት ከተማ አሥተዳደሩ ከገጠመው ችግር አንጻር መዘግየቱ ተገቢ ነው ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እስካሁን ማኅበራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ማኅበራት ዛሬ የብሎክ እጣን እንዲያወጡ በበርካታ ትግል ውስጥ ማለፉንና በበርካታ ችግሮች ውስጥ ያለፈ በመኾኑ እንደዘገየ አብራርተዋል።
ከቦታ ጥያቄ ጋር ተያይዞ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች መኖራቸው ለመዘግየቱ አንድ ምክንያት እንደኾነ አብራርተዋል። ሕገወጥ በኾነ መልኩ ለመጠቀም የሚሯሯጡ ደላላዎችና ሌሎች አካላት ቁጥር በርካታ እንደኾነም ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ያብራሩት።
ዜጎች ፍትሐዊ የኾነ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ኹሉም ሕገወጦችን በጋራ መታገል እንዳለባቸው ዶክተር ድረስ ጠይቀዋል። በቀጣይም ዜጎች በተመሳሳይ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ልክ ዛሬ የብሎክ እጣ እንደወጣላቸው ማኅበራት ቀና ተባባሪ መኾን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዶክተር ድረስ እንዳሉት ዛሬ የብሎክ እጣ የወጣላቸው ማኅበራት በአጭር ቀናት ውስጥ የብሎክ ሽንሸናና የማጣራት ተግባር ይፈጸማል። ከማጣራት ሥራው ጎን ለጎን ሌሎች ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው ያብራሩት።
ከተማ አሥተዳደሩ የአርሶ አደር ልጆችንም የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ተጠቃሚ በማድረግ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ዶክተር ድረስ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን መለሰ ከአሁን በፊት ቦታ በተረከቡ ማኅበራት የማጣራት ተግባር በማከናወናቸው በርካታ ሕገወጦች እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል። ወደፊትም ቢኾን ሕጋዊነትን ለማረጋገጥ የማጣራት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኀላፊው አስገንዝበዋል።
ኀላፊው መደራጀት እንደሚቀጥልና እግዱ በቅርብ ቀን ሊነሳ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። አቶ ፈንታሁን እንዳሉት ወደ ፊት የሚደራጁ ማኅበራት መሬት በማደል ብቻ ሳይኾን በአፓርታማ ሊኾን እንደሚችል አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!