
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ ሂደቶች ነበሩት። ዩኒቨርሲቲውን ለመመስረት እንደመሠረት ድንጋይ ሆነው ካገለገሉት ኹነቶች መካከል የቀድሞው የባሕርዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት መቋቋሙ ነበር።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በሐምሌ ወር 1951 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሶቪዬት ኅብረት ባደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት፤ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከኒኪታ ክሩቸቭ ጋር ተገናኝተው ከደረሱባቸው ስምምነት መካከል አንዱ ወጪውን ሙሉ በሙሉ በሶቪዬት ኅብረት መንግሥት የሚሸፈን አንድ ዘመናዊ የፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት በባሕርዳር ከተማ መገንባት ነበር። ግርማዊነታቸው ታኅሣሥ 21 ቀን 1954 ዓ.ም የመሠረት ድንጋዩን አስቀምጠው ሰኔ 4/1955 ዓ.ም መርቀው እንደከፈቱት በኮንፈረንሱ ተወስቷል።
የቀድሞ ተማሪዎቹም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ከፍተኛ ኀላፊነቶች ላይ የሚገኙና ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ በአዲስ አበባ የፖሊ ፔዳ እና ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል አዘጋጅ አሉሚኒ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው ተናግረዋል።
1992 ዓ.ም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚል ስያሜ አግኝቶ በአወቃቀርም በተማሪ ቅበላም በትምህርት ክፍልም ከፍ እያለ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን 13 የምርምር ማዕከላት አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል ተብሏል።
ይህንን መነሻ በማድረግ የዚህ ኮንፈረስ መዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያቶች ሰኔ 2015 ዓ.ም ባሕር ዳር በሚከናወነው ክብረ በዓል ለይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ የቀድሞ ምሩቃን መሳተፍ እንዲችሉ ቅስቀሳ ለማድረግ በማስፈለጉ፤ የሦስቱም ተቋማት የቀድሞ ምሩቃን በየተሰማሩበት የሥራ ዘርፎች አኩሪ እና ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኙ ተግባራትን ያከናወኑ እና በማከናወን ላይ የሚገኙ በመሆኑ ከእነርሱ ውስጥ የተወሰኑትን በመምረጥ የስኬት ታሪኮቻቸውን በዚህ ኮንፈረስ ለይ ለማስተዋወቅ፣ እነዚህ የስኬት ታሪኮች ወጣቱን ትውልድ ለተሻለ ስኬታማ ሥራዎች የሚያነሳሱ ስለሆነ ጠቃሚ ልምዶችን ለማኅበረሰቡ በስፋት ለማስተዋወቅ፣ የቀድሞው ምሩቃን ተበታትነው የሚገኙ ስለሆነ ተደራጅተው ለሀገር እና ለትውልድ በተለይም ለባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መጠንከር ጠቃሚ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲረዳቸው፣ የአሉምኒ ምስረታ ሃሳቦችን አቅርቦ ውሳኔ ለመድረስና በአጭር ጊዜ ውስጥ የቀድሞው ምሩቃን አሉምኒ ለመመስረት ያለመ መሆኑን ኢንጅነሩ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) “ባሕርዳር ከተማና ዩኒቨርሲቲያችን እነዚህን የመሠሉ እንቁ ዜጎች የወጡበት ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ኩራት ይሰማዋል።ለ60ኛ ዓመቱ መከበር ለምታደርጉት አስተዋፅኦም እናመሰግናለን ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው እንደከዚህ ቀደም በድግስ ሳይሆን በተጨባጭ ፕሮጀክት በዓሉን እንደሚያከብር ዶክተር ፍሬው ገልጸዋል።
በመርሃግብሩ የቀድሞ ተማሪዎች የትና በምን ሁኔታ እንዳሉ፣ እንዲሁም ለከተማዋ፣ ለዩኒቨርሲቲውና አጠቃላይ ለሀገር ምን ሊያበረክቱ ይችላሉ በሚል መወያያ ጽሑፎች ቀርበዋል።
ኮንፈረንሱ የቀድሞ ተማሪዎች አልሙናይ በብሔራዊ ደረጃ በማቋቋም ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!