
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ፤ ሀገራችን ብሎም ክልላችን የሰው ልጆች በሚፈልጉት ጸጋ የተሞላች ብትኾንም በሥግብግብ ነጋዴዎች ወዳልተፈለገ መንገድ እየሄድንበት ያለው መንገድ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ይሁን በዓለም በቂ መሠረተ ልማት ባልነበረበት ዘመን የሲራራ ነጋዴ ከቦታ ቦታ ምርት በማዘዋወር ኀላፊነቱን ይወጣ እንደነበር አንስተዋል። አሁን ሳያመርት ገዝቶ ሳይገዛ ሸጦ ትርፍ የሚያገኝበት ዘመን ላይ ደርሰናል፤ ነገር ግን እየተፈጠረ ያለውን ምቹ ኹኔታ ወዳልተፈለገ መንገድ በመጠምዘዝ ሕገወጥነትን እንደ ሕጋዊነት ለመውሰድ የሚፍጨረጨር አካል መኖሩ የተፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ ወዳልኾነ መንገድ እየጠመዘዘው መኾኑን አንስተዋል።

ይኽን ልናስቆምበት የምንችልበትን ሥርዓት ቢሮው ሊፈጥር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጤናማ የንግድ ሥርዓት በመዘርጋት አምራቹን፣ ሸማቹን እና ነጋዴውን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል። በገበያ ሥርዓት የሚመራ የንግድ እና ግብይት ሥርዓት መፈጠር አለበትም ብለዋል።
አምራቹ ማኅበረሰብን ተጠቃሚ የማያደርግ፣ ለሸማቹ የተጋነነ ዋጋ በማቅረብ የሚያማርሩ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ እስከታች ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!