
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ አዘጋጅነት በትብብር ሥልጠና አተገባበር ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ክልል አቀፍ የምምክክርና ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሔደ ነው።
“ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኀይል ልማት ለዘላቂ የሥራ እድል ፈጠራ” የመድረኩ መሪ መልእክት ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀንበር (ዶ.ር) ሥራ አጥነት መሠረታዊ ችግር ኾኗል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኢንዱስትሪዎች የበቃና የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ይስተዋላል ብለዋል።
ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሰለጠነ የሰው ኀይል በመፍጠር በኩል የማይተካ ሚና አላቸው፣ይኹንና ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት ልክ የበቃ የሰው ኀይል ያለማፍራታቸው ጉዳይ ግን ትኩረት የሚያሻው እንደኾነ አስረድተዋል።
እናም ” የሠለጠነ የሰው ኀይል ለመፍጠር ሥንሠራ ገበያው የሚፈልገው ስለመኾኑ ትኩረት መስጠት ይገባል” ነው ያሉት ዶክተር ጌታቸው።
ቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑ ወጣቶች ሥራ ፈላጊ ሳይኾኑ ሥራ ፈጣሪና የኢንዱስትሪዎችን ችግር የሚፈቱ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
ሠልጣኞች እውቀቱም ክኅሎቱም እንዲኖራቸው ከኢንዱስትሪዎችና ከግሉ ባለሃብቶች ጋር የትብብር ሥልጠናዎችን በማጎልበት ችግሩን መፍታት እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተር ጌታቸው፤ የዛሬው መድረክም በዚህ ጉዳይ ፋይዳው የጎላ እንደኾነም ተናግረዋል።
ብቁና ፣ተወዳዳሪና ለገበያው የሚመጥን የሠለጠነ የሰው ኀይል ለመገንባት ሁሉም በኀላፊነት እንዲሠራም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሥራ አጥነት ቁጥር 70 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
ቢሮው 1ነጥብ 2 ሚሊየን ሥራ አጥ የሰው ኀይል እንደመዘገበም ነው የተናገሩት።

ከተመዘገቡት ሥራ ፈላጊዎች መካከል ከ106 ሺህ በላይ የሚኾኑት ምሩቃን መኾናቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ነው ያሉት።
በየጊዜው የሚመረቁ የኮሌጅ ምሩቃን ሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፣ በሌላ በኩል ኢንዱስትሪዎችና ገበያው የሚፈልገው የሠለጠነ ብቁ የሰው ኀይል እጥረት መኖር በጋራ መግባባት ላይ መሥራት እንደሚጠይቅ ያመላክታል ብለዋል።
እንዲህ አይነት የትብብር ሥልጠናዎችን በእቅድ መምራት እና ቅንጅታዊ አሠራርን ማበጀት ስብራቱን የሚፈታ ይኾናል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።
ዘጋቢ፦ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!