
ባሕር ዳር:መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የከተሞችን ዝምንና በማሳደግ ለነዋሪዎች ምቹና ተመራጭ በማድረግ ረገድ ቴክኖሎጅን የተላመደ አሠራር ላይ ትኩረት ስለመደረጉ ይነገራል፡፡
እንደ ሀገር “በከተሞች ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ በፕላን እንዲመሩ ምቹ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸውና በከተሞች ዕድገት ዙሪያ ወጥ ግንዛቤ አለመኖር በዜጎች ላይ የመልካም አሥተዳደር ችግር እየፈጠረ ስለመኾኑም ነው ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
እንደ መፍትሔም በሀገሪቱ በተመረጡ ከተሞች ከየሀገራቱ ስልጡንና ተመራጭ ከተሞች ልምድን በመቀመር የ“ስማርት ሲቲ” ጽንስ ሃሳብን ተግባራዊ በማድረግ እየተሠራበት ይገኛል፡፡
“ስማርት ሲቲ” ከተሞችን ማራኪና ሳቢ ፣ቀልጣፋ የአሠራር ሥርዓት፣ዲጅታል ቴክኖሎጂን በመጠቀምም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ዕውን በማድረግ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹና ተመራጭ ከተማን የመገንባት እሳቤ ነው፡፡
ባሕር ዳር ከተማም የ“ስማርት ሲቲ” ትግበራን ዕውን ለመድረግ ጅማሮ ላይ ስለመኾኗ ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዶክተር ድረስ ሳህሉ የተናገሩት፡፡ ለዚህም ለከተማ አሥተዳደሩ አመራሮች እና የተቋም መሪዎች የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ሥልጣና እየተሰጠ ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ዴኔሮ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ልማትና ምሕንድስና ትምህርት ዘርፍ ዲን እንዲሁም በከተማ ልማት ዲዛይን ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽዱ፣ ውብ ፣ለነዋሪዎቿ ምቹና ተመራጭ የኾነች ፣ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ የሚተገበርባት እና ከብልሹ አሠራር የጸዳች ዘመናዊ ከተማን መገንባት ዘመኑ የሚጠይቀው የከተሞች መወዳደሪያ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
በዕውቀት እና በመረጃ ላይ ተመስርቶ “ስማርት ሲቲ” ትግበራን ዕውን ማድረግ ደግሞ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ስለመኾኑ ነው የሚያስረዱት፡፡
ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጅ መሰረተ ልማት መገንባት ፦ ለመረጃ ፣ ለአገልግሎት አሠጣጥ ቅልጥፍና፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሳይ ፣ ብልሹ አሠራርና ሙስናን የሚያጋልጥ የቴክኖሎጅ ውጤቶችን የሚጠቀም ከተማ መገንባት ነው “ስማርት ሲቲ” ትግበራ ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል። ለዚህ ግን የነቃ አመራርና ባለሙያ፤ ስልጡን ማኅበረሰብ አስቀድሞ መፍጠርን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
ከተሞች ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታ የሚነሳባቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመለየት አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣የመልካም አሥተዳደር ፈተና የኾኑ ችግሮችን መፍታት፣ብልሹ አሰራርንና ሙስናን መታገል ይቻላል ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጅ ዓለምን ወደ ከተማነት እየቀየረ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ፣ አሁን ላይ በዓለም ላይ 60 በመቶ በላይ ሀገራት የከተሜነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ ኢትዮጵያ ግን ከተሜነቷ 20 በመቶ ላይ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡
ከሁሉም በፊት ግን ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ዲጅታል ቴክኖሎጂ ብቻውን ስማርት ሲቲ ትግበራን ለማረጋገጥ በቂ አይደለምና ርዕይና ዕቅድ ያለው አመራርና ባለሙያ ፤ የዘመኑን ዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልገሎት የሚረዳና የሚጠቀም ዜጋ መፍጠር ይገባል ባይ ናቸው። በከተማ ዝምንና የነዋሪዎችን አኗኗር ማሻሻል እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ስማርት ሲቲ ትግበራን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እንደተጀመረ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተናግረዋል፡፡ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከተሞች ልምዶችን በመቅሰም የመጡ ተሞክሮዎችን ወደተግባር ለመቀየርም ከሕግና ከመመሪያ ጋር ማወዳጀት፣አስተሳሰብ ላይም ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ነው ብለዋል ከንቲባው፡፡ ከባለሃብቶች እና አጋር አካላት ጋርም ቅንጅታዊ አሠራር ተዘርግቷል ነው የተባለው፡፡
በከተማዋ የመዘጋጃ ቤት አሠራሮችን፣ የሊዝ ክፍያን፣የባንክ እገዳን፣የካርታ አሰራርን ፣የመሬት መረጃ አያያዝን፣ የፍርድ ቤት እገዳን እና ሌሎች ጉዳዩች ላይ በተወሰኑ ክፍለከተሞች ሥራን በዲጂታል ቴክኖሎጅ የሙከራ ትግበራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡
እንደ ሀገርም የስማርት ሲቲ ትግበራው ሙከራ ባሕር ዳር ከተማን ያካተተ በመኾኑ በከተማዋ ኢትዮ-ቴሌኮም በዲጂታል ቴክኖሎጅ ግንባታው በስፋት እየሰራ ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!