የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት ሥራ ጀምሯል፡፡

1073

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ስራ ጀምሯል፡፡

ሚያዚያ 2011 ዓ.ም ገደማ የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻና ማሻሻል በማድረግ እንቅስቃሴ የጀመረው የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በ2012 ዓ.ም ሥራ እንደሚጀመር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ትምህርት ቤቱ በተባለለት ጊዜ ወደ ሥራ መግባቱን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሥነ ልቦና ትምህርት ክፍል ተጠሪና የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ደመቀ ብናልፍ (ዶክተር) ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ሥራ ጀምሯል፡፡

በማኅበረሰቡ ጥብቅ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንቅስቃሴ የጀመረው አዳሪ ትምህርት ቤቱ በዩኒቨርሲቲው አስፈጻሚነት ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ “የአካባቢው ማኅበረሰብ ምርጫና የሁሉም ነገር ቀዳሚው ነገር ትምህርት ነው” ያሉት ዶክተር ደመቀ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሳካት ያስችል ዘንድ በአካባቢው ማኅበረሰብና በዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች የጋራ ጥረት እውን እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ሥራ ሲገባ 60 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን እንደተቀበለም ዶክተር ደመቀ አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎችን ለመለየት ከ7ኛ ወደ 8ኛ ክፍል ያለፉበት የክፍል ፈተና ውጤት፣ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ውጤትና የመግቢያ ፈተና ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ዶክተር ደመቀ አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲመረጡ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ደብዳቤ አስገብተው እንደነበርም ዶክተር ደመቀ አስታውሰዋል፤ ነገር ግን ደብዳቤው በተፈለገው ልክ ለሁሉም አካባቢዎች ሳይዳረስ በመቅረቱ ትምህርት የጀመሩት ከምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተውጣጡ ተማሪዎች ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በአማራ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን አወዳድሮ እንደሚያስተምርም አረጋግጠዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚማሩባቸውን ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በተመለከተም አስቀድሞ እየሠራ እንደሆነ ዶክተር ደመቀ አስታውቀዋል፡፡ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በተለይም ከገጠር አካባቢ ለሚመጡ ተማሪዎች አዲስ ተስፋ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ደመቀ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመላክተዋል፡፡

ጅማሮውን ለማጠናከርና በስፋት ለመሥራት የኅበረተሰቡ፣ የምሁራን፣ የባለሀብቶችና የመንግሥት እገዛ እንደሚያስፈልግና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ “ሀገርን በሁሉም ዘርፍ ለማልማትና ለማበልጸግ አዕምሮን ማልማት ይቀድማል” ያሉት ዶክተር ደመቀ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ድጋፍ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመክፈት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችንና በኢንጂነር ጸደቀ ይሁኔ አማካኝነት የተገነባው የአዳሪ ትምህርት ቤት ደሴ ላይ ሥራ መጀመሩን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን አዳሪ ትምህርት ቤት የግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታና ፍጥነት እንደሚገኝ በቅርቡ መዘገባችንም ይታወሳል፡፡ አልማ የሚያስተባብራቸው የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በባሕር ዳር፣ ጎንደርና ሌሎችም ከተሞች የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleበወረኢሉ ወረዳ የባዮጋዝ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ልምድ እየተጎበኘ ነው፡፡
Next article‹‹መንገዱ ከዲዛይኑ ውጭ እንዲሠራ ተደርጎብናል›› ሲሉ የቅራቅር ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡