የባሕር ዳር ከተማን የውኃ አቅርቦት ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ አስታወቀ።

89
ባሕር ዳር:መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የቱሪስት ፍሠት የምታስተናግደው ባሕር ዳር የውኃ ችግሯ ያልተፈታላት ከተማ ናት። የከተማዋን የውኃ ችግር ለመቅረፍ የውኃ ተቋማት እየተገነቡ ነው፡፡
በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ወንድአጥር መኮንን የባሕር ዳር ከተማን የውኃ ችግር ለመቅረፍ በ743 ሚሊዮን ብር ወጭ እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በመጭው ግንቦት ወር ይጠናቀቃሉ ብለዋል።
በጃፓን መንግሥት ድጋፍ በ650 ሚሊዮን ብር እና በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ በ93 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነቡ ያሉት ሁለት ፕሮጀክቶች በቅርቡ ተጠናቀው አገልግሎት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የተገነቡ የውኃ መሠረተ ልማቶች የኅብረተሰቡን ከፍተኛ የውኃ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው የገዘፈ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየቱን አቶ ወንድአጥር አንስተዋል።
ከመልካም አሥተዳደር ችግር በተጨማሪ በቱሪስት ፍሠቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰቡን የውኃ ጥያቄ ለመፍታት የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ከጃፓን መንግሥት ባገኘው ድጋፍ እየተገነቡ ያሉ የውኃ ተቋማት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና በጀት እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በ650 ሚሊዮን ብር በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የሚገነባው የውኃ ተቋም አንዱ ነው።
በጃፓን መንግሥት እየተገነባ የሚገኘው የውኃ ፕሮጀክት ከ25 እስከ 30 ዓመት እንደሚያገለግል በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል። ፕሮጀክቱ 96 በመቶ ተጠናቅቆ የፊታችን ግንቦት ወር ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል አቶ ወንዳጥር። በፕሮጀክቱ 5 አዳዲስ የውኃ ጉድጎዶች የተቆፈሩ ሲሆን 4 ነባር ጉድጓዶችን ወደ ሲስተሙ ያስገባልም ተብሏል።
በአዲስ የተቆፈሩት 5 ጉድጓዶች ብቻ በሴኮንድ 192 ሊትር ውኃ ለአካባቢው ይደርሳል ነው ያሉት። ይህ ፕሮጀክት በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ከአሁን በፊት አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩት 4 ጉድጓዶች ጋር ተደምሮ በሴኮንድ 350 ሊትር ውኃ ለማኅበረሰቡ ይደርሳል።
የቀጠናውን የውኃ ሽፋንም ወደ 100 ፐርሠንት ያሳድጋል ብለዋል። ፕሮጀክቱ ባለ 4 ሚሊዮን ሊትር እና ባለ 1 ሚሊዮን ሊትር ውኃ መያዝ አቅም ያላቸው የውኃ ጋኖችን ገንብቶ አጠናቅቋል። ውኃን ከተለያዩ ጉድጓዶች ተቀብለው ወደእነዚህ ጋኖች የሚልኩ ባለ 1 ሚሊዮን ሊትር፣ ባለ 700 ሺህና ባለ 200 ሺህ ሊትር የማቀባበያና የውኃ ማከሚያ ጋኖችም ተገንብተውለታል።
በመጭው ግንቦት ወር ወደ አገልግሎት እንደሚገባ የሚጠበቀውና አሁን 96 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት ባለ ከፍተኛ አቅም ፓምፖች የተገጠሙለትና ከጉድጓዶች ወደ ጋኖችና እንዲሁም ከጋኖች ወደ አቅርቦት ሥፍራዎች የሚያደርስ የ14 ኪሎ ሜትር የዋና የውኃ መስመር፣ ከዋናው መስመር ተቀብሎ ውኃን ወደየቤቶች የሚያሠራጭ ደግሞ የ27 ኪሎ ሜትር የሥርጭት መስመር በጥቅሉ የ42 ኪሎ ሜትር ዝርጋታ መከናወኑን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የውኃ ስርጭትን በሥርዓት ማቅረብ የሚያስችልና የውኃ ብክነትን የሚቆጣጠር ቴክኖሎጅም ተሰርቶለታል።
ከአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ውጪ ባሉ የከተማዋ ክፍሎች ያለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታትም በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ በ93 ሚሊዮን ብር ወጪ በአማራ ውኃ ሥራዎች ድርጅት ተቋራጭነት ይባብ አካባቢ ከሚገኘው የጥቁር ውኃ ምንጭ ወደ ከተማው የሚያደርስ የ12 ኪሎ ሜትር የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው የዋና የውኃ መስመሮችን የመቀየር ሥራም ተጠናቋል። የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው የኤሌክትሮ ሜካኒካል እቃዎችን የመቀየር ሥራም ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
የዚህ ፕሮጀክት አፈጻጸም 99 በመቶ ደርሷል። የኤሌክትሮ ሜካኒካል ገጠማው እንደተጠናቀቀ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም አቶ ወንድአጥር መኮንን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የአማራ ክልል አሁን ላይ የተረጋጋ ነው” ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleየአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ መጋቢት 01/2015 ዓ.ም ዋና ዋና ዜናዎች፦