
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሻቸው መንግሥት መንግሥትነቱ የሚረጋገጠው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ሲያስጠብቅ ነው ብለዋል።
በምላሻቸው የአማራ ክልል በችግር ውስጥ የቆዬ ክልል እንደነበር አስታውሰዋል። ከሕዝቡ ጋር በተሠራው ሥራም አሁን ባለው ሁኔታ የተረጋጋ ክልል ሆኗል ነው ያሉት። ይሁን እንጅ አሁንም ሰዎችን የሚያግቱ፣ የሚዘርፉ፣ በከተማ ላይ ሰላምና ደኅንነትን ለማወክ የሚጥሩ አካላት እንዳሉ ጠቅሰዋል። የክልሉ የፀጥታ ኃይል የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለ እረፍት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፀጥታ ኃይሉ እያደረገው ላለው አስተዋጽኦ ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝበዋል።
ያለኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወንጀልን መከላከል አይቻልም ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ለሰላምና ደኅንነት ሥራ ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ ክልሉ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም እና ለሌሎች የልማት አማራጮች አስተማማኝ እንዲሆን በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በሠራው ጠንካራ ሥራ የሰላምና ደኅንነት ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ ሰላም መመለሳቸውንም አስገንዝበዋል።
በክልሉ በፅንፈኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በሚመለከት በተሠራው ሥራ ፅንፈኛ የቅማንት ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም በተሠራው ሥራ ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን እና በአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መፈጠሩን አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግሥት ከሕወሃት ታጣቂዎች ጋር አብረው ሲዋጉ ከነበሩ የአገው ሸንጎ አባላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም አንስተዋል።
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በሸኔ ታጣቂዎች ምክንያት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውን ነው ያስገነዘቡት። በጥቂት ግጭት ፈጣሪዎች አብሮ የኖረ ሕዝብ ከሰላማዊ ሕይወቱ ሊደናቀፍ እንደማይገባውም ጠቅሰዋል። የተባበረ እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እንሠራለን ብለዋል። ተባብረን ከሠራን በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎችን መፍታት እንችላለን ነው ያሉት።
ሕገወጥ ንግድን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን መከላከል እንደሚገባም አንስተዋል። የምክር ቤት አባላት የሰጧቸው ግብዓቶች በትኩረት እንደሚታዩም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!