20 ኢንቨስተሮች በስኳር ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል።

79
ባሕር ዳር:መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ወደ ግል ሴክተር የሚዞሩ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን በመግዛት በዘርፉ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የለውጥ ሥራዎች አማካሪ ወይዘሪት ሂንጃት ሻሚል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የግል ኢንቨስተሮች መሳተፍ እንደሚችሉ በተደረገው ጥሪ መሠረት ከ20 በላይ የሚሆኑ የግል ተቋማት መሳተፍ እንደሚፈልጉ ከወዲሁ አሳውቀዋል።
በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮችን ፍላጎት ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቡድን በማዋቀር የግል ተቋማቱ ያቀረቧቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ተመልክቷል ሲሉ አማካሪዋ ተናግረዋል።
ፋብሪካዎቹ ለሀገር የሚያስገኙትን ትርፋማነት በተመለከተ እና ኢንቨስተሮቹ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ የፕራይቬታይዜሽን ሂደቱን ያማከለ ምክረ ሀሳብ እየተዘጋጀ መሆኑንም አመላክተዋል።
እንደ አማካሪዋ ገለጻ፤ ወደ ግል የሚዛወሩት የስኳር ፋብሪካዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፣ የማምረት አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ፣ ከማምረት ሂደት ጋር በተያያዘ መንግሥት ምን ዓይነት ፖሊሲ ሊያወጣ ይችላል፣ ሙሉ በሙሉ በግል ነው ወይስ በከፊል ሆኖ በሽርክና መሥራት አለባቸው የሚለውን ጉዳይ የያዘ ሰነድ እየተዘጋጀ ይገኛል።
በሚቀርበው ምክረ ሀሳብ መሠረት መንግሥት ምላሽ ከሰጠበት በኋላ በሚቀጥሉት አምስት ሳምንታት ውስጥ የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ለማዞር የሚረዳ ጨረታ እንደሚወጣ አማካሪዋ አስታውቀዋል።
ፍላጎት ያሳዩ ኢንቨስተሮች ስለፋብሪካዎቹ ሁኔታ መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል ያሉት ወይዘሪት ሂንጃት፤ የተወሰኑት ኢንቨስተሮች ስኳር ፋብሪካዎቹ የሚገኙበት ቦታ ድረስ በመሄድ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
አማካሪዋ እንዳስታወቁት፤ የተመረጡት ስምንት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ሴክተር እንዲዛወሩ መንግሥት ያቀደበት ዋነኛ ምክንያት ፋብሪካዎቹ አመርቂ ውጤት ማምጣት ስላልቻሉ እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ሙሉ በሙሉ ስላላሟሉ ነው።
ፋብሪካዎቹ ወደ ግል አምራቾች ሲዛወሩ የተሻለ አቅም እንደሚፈጠርላቸውና ምርታማነታቸው እንደሚያድግ ይታመናል ብለዋል።
ፋብሪካዎቹ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ስለሚፈልጉ እንዲሁም በግሉ ዘርፍ የብዙ ጊዜ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ቢሳተፉበት ውጤታማ ይሆናሉ የሚል ዕሳቤ እንዳለም አስረድተዋል።
የተመረጡት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግሉ ዘርፍ ሲዞሩ በተለያዩ ሀገራት በዘርፉ ልምድና ካፒታልን ያካበቱ ኢንቨስተሮችም አብረው ይመጣሉ። ይህም በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፍ የካበተ ልምድ ካላቸው ሀገራት ዕውቀት፤ ክህሎትና ካፒታልን ለመጋራት ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል ለመልሶ መቋቋም ሥራ 1 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ገለጹ።
Next article“የአማራ ክልል አሁን ላይ የተረጋጋ ነው” ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)