በአማራ ክልል ለመልሶ መቋቋም ሥራ 1 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ገለጹ።

131
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እየሠጡ ነው።
ርእሰ መሥተዳድሩ በምላሻቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች አበረታች ለውጥ እየታየባቸው መኾኑንም አንስተዋል። በመስኖ ልማት ዙሪያ የሚታዩትን ችግሮች መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። የመብራት ችግር በክልሉ መኖሩንም ገልጸዋል። የመብራት ችግርን መፍታት ይገባልም ነው ያሉት።
በክልሉ የመልሶ መቋቋም ሥራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል። በተመደበው 1 ቢሊዮን ብር የመልሶ መቋቋም ሥራ እየተሠራ ነው፣ ከፌዴራል መንግሥት ለመልሶ ማቋቋም የሚውል ገንዘብ በቅርቡ እንደሚለቀቅ ይጠበቃልም ብለዋል። ክልሉ በመልሶ ማቋቋም ረገድ ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ጉዳቱ ተጠንቶ በመፅሐፍ ታትሟል ነው ያሉት።
ገቢ በመሰብሰብ ረገድ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። የተሰበሰበው ገቢ ለተፈለገው ዓላማ መዋል ይገባዋልም ብለዋል። ወረዳዎች በጀትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ወረዳዎች ላይ ትክክል ያልሆነ የበጀት አጠቃቀም መኖሩንም አንስተዋል። ያለ ፍላጎት የሥራ ቅጥር የሚቀጠርባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ወረዳዎች በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት። የሕዝብን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ይገባልም ብለዋል።
ለሕዝብ አገልግሎት መሥጠት የሚችል የሰው ኃይል ብቻ መቀጠር እንዳለበትም ተናግረዋል። ገቢውን በአግባቡ በመሰብሰብ ወጪውን ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት። ወጪን በቁጠባ መጠቀም ካልተቻለ ከፍተኛ የኾነ የበጀት እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልም አሳስበዋል።
ጉቦ የሚቀበሉ የሥራ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን ማጋለጥ ይገባል ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ ሌባን ሌባ ሊለው እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ሙስናን ለመከላከል የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ኮሚቴው በሚያደርገው ማጣራት ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት። ሕዝቡ ሙስናን ለመከላከል በሚደረገው ሂደት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። በሙስና ትግሉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት አንድ ሚሊዮን ዮሮ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
Next article20 ኢንቨስተሮች በስኳር ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል።