
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛው ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ሲቀጥል የፈጻሚ ተቋማት ኀላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ እየሠጡ ነው። በግብርናው ዘርፍ ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ የሠጡት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በግብርናው ዘርፍ ባለፉት ወራት አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል። እንደ ሀገር ከተመረተው የስንዴ ምርት በአማራ ክልል አንድ ሦስተኛው መመረቱንም ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት ከበፊቱ የተሻለ መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑንም አስታውቀዋል።
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። የስንዴ ምርት የግብርና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት መገለጫ ነውም ብለዋል።
የማዳበሪያ እጥረት እንደ ሀገር መኖሩንም ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ በትኩረት መሠራቱንም ተናግረዋል። ለክልሉ የሚመጣውን ማዳበሪያ ተከታትሎ በማድረስ ረገድ እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በክልሉ የዘር አቅርቦት ችግር እንደነበር ያነሱት ኀላፊው አሁን ላይ የዘር አቅርቦት ችግሮችን እየፈቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የከተማ ግብርና በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።
በክልሉ የሜካናይዜሽን ሥራ ላይ ቢሮው በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ሜካናይዜሽን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።
ሕገወጥ ደላላዎች በግበርና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!