ባለፈው ሩብ ዓመት ብቻ 1ሺህ 221 ፈቃደኛ ኢትዮጵውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

160

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) አሜሪካ በግድቡ ጉዳይ ለሦስቱ ሀገራት ያደረገችው ጥሪ ዓላማው ውይይት እንጂ ድርድር አለመሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም የዜጋ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ሰሞኑን በሊባኖስ አለመረጋጋት መከሰቱን ተከትሎ ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ በሀገሪቱ የሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅ እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በሊባኖስ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልተፈጠረባቸውም ነው የገለጹት፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የኢትዮጵያ እና የሊባኖስ መንግሥታት በሥራ እና በዜጎች መብት ጥበቃ ላይ በቅርቡ ሁለት ሥምምነቶችን ሊፈራረሙ እንደሆነ ነው አቶ ነቢያት ያስታወቁት፡፡

በጅቡቲ ታጁራ እና ኦቦክ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሠራ ስለመሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፍልስተኞች ክብራቸው እና ጤንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው በፈቃደኝነት እንዲመለሱ በጅቡቲ የኤፌዴሪ ኤምባሲ ከጅቡቲ መንግሥት እና በጅቡቲ ከዓለማቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሆነም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡

በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ተታልለው ሳዑዲ ዐረቢያን መዳረሻቸው ለማድረግ ጅቡቲን አልፈው የመንን ለማቋረጥ ከሚሞክሩ ኢትዮጵውያን መካከል ባሳለፍነው ሩብ ዓመት ብቻ 1ሺህ 221 ፈቃደኛ ኢትዮጵውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አቶ ነቢያት አስታውቀዋል፡፡

የፖለቲካ ዲፕሎማሲን በተመለከተም የኢትዮጵያን ጥቅምና መልካም ግንኙነት የሚያስጠብቁ ግንኙነቶች ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስመለካሄዳቸው ነው ያስታወቁት፡፡

የኢትዮጵ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በሩሲያ ሶቺ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ባደረጉት ውይይት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረውና በየምክንያቶች ሲስተጓጎል የቆው የቴክኒክ ውይይት እንዲቀጥል መግባባት ላይ እንደተደረሰ ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡ በቴክኒክ ውይይት ሂደቱ አለመግባባት ቢኖር እንኳን በመሪዎች ደረጃ ለማየት የፖለቲካው አግባብ ዝግ እንዳልሆነም አስታውቀዋል፡፡ ግድቡን በተመለከተ ለኢትዮጵያ፣ለግብጽ እና ለሱዳን አሜሪካ ያደረገችው ጥሪም ለውይይት እንጂ ለድርድር እንዳልነበር አቶ ነቢያ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያም ዋናው ጉዳይ የቴክኒክ እንደመሆኑ መፍትሔውም የቴክኒክ ነው የሚል እምነት እንዳላትም ነው በመግለጫቸው ያመላከቱት፡፡

ኢኮኖሚን በተመለከተም በጣልያን እና በፈረንሳይ የቢዝነስ ፎረሞች እንደተካሄዱ አስታውሰዋል፡፡ በዚህም በመንግሥት ተወካዮችና በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለተሠማሩ የጣሊያንና የፈረንሳይ ባለሀብቶች ሰፊ ማብራሪያ እንደተሰጠ ነው የተናገሩት፡፡ በሁለቱ ሀገራት ኩባንያዎችም አወንታዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት ተደርጓል ነው ያሉት አቶ ነቢያት፡፡

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ – ከአዲስ አበባ

Previous articleወጣቱ ከግጭት ተግባር ተቆጥቦ በፍሬያማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ስምሪት ላይ ማተኮር እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
Next articleበወረኢሉ ወረዳ የባዮጋዝ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ልምድ እየተጎበኘ ነው፡፡