
ባሕርዳር: የካቲት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሕግና ሥርዓት ያልተመራ የገበያ ሥርዓት በመኖሩ የዋጋ ንረቱ ከፍ ማለቱን ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) ተናገረዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ እየሠጡ ነው። በግብርናው ዘርፍ በትኩረት መሥራታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። በተመረጡ ሰብሎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል። በአማራ ክልል በቂ ምርት አለ፤ ነገር ግን ገበያው አሻቅቧል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በገበያ ሕግ የማይመራ የገበያ ሥርዓት በመኖሩ የዋጋ ንረት መኖሩንም ገልጸዋል። በምርት መጠን ላይ መጨመር እንጂ መቀነስ አለመታየቱንም አስረድተዋል፡፡
የክልሉን የምርት ፍላጎት ማርካት አስፈላጊ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከዚያ ያለፈውን ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባም ገልጸዋል። አርሶ አደሩ በዚህ ልክ መሸጥ አለብህ ሊባል አይገባም፤ ገበያ በወሰነው መሠረት ሊሸጥ ይገባልም ነው ያሉት። ምርትና ምርታማነትን መጨመር ለነገ የሚባል ጉዳይ አለመኾኑንም ነው ያስረዱት። በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል። በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉም በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል። በክልሉ የመጀመሪያው የሆነው የሲሚንቶ ፋብሪካ በቀጣይ እንደሚጀምርም ተናግረዋል። ይህም በክልሉ የሚስታዋለውን የሲሚንቶ ችግር ለመቅረፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት። በርካታ ባለሃብቶች በዓባይ ሸለቆ አካባቢ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመክፈት እየጠየቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥትም አልሚ ባለሃብቶችን ይደግፋል ነው ያሉት።
በማዕድን ዘርፉም በትኩረት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት። በአማራ ክልል ተስፋ ሰጪ የማዕድን ሃብት መኖሩንም ገልጸዋል። በማዕድን ዘርፉ እየተሠሩ ያሉ ጥናቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ለመግባት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!