
ባሕር ዳር፡ የካቲት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የ2015 ዓ.ም ዋና ተግባር የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መኾኑ የቢሮው ኀላፊ አቶ መሐመድ ያሲን ለክልሉ ምክር ቤት ተናግረዋል።
አቶ መሐመድ የተጀመሩ ነባር የመንገድ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመሩም ተናግረዋል። ከተያዘላቸው ጊዜ በላይ የዘገዩ የክልሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚጠይቁት ተጨማሪ በጀት ተመድቦም ቢኾን ለማጠናቀቅ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለረጅም ጊዜ የተጓተቱ እና ከፍተኛ የበጀት ጭማሪ የጠየቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው፤ ከተቋራጮች ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቁ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ቢሮ ኀላፊው የተጀመሩ መንገዶች ክረምት ከመግባቱ በፊት ተጠናቀው ከሰኔ 30/2015 ዓ.ም በፊት ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
አቶ መሐመድ በጦርነት ምክንያት የተቋረጡ 30 በፌደራል የሚሠሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ ገልጸዋል። መልሰው የተጀመሩት አብዛኞች ፕሮጀክቶች በመልካም አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። 14 የሚኾኑት ፕሮጀክቶች እንደገና ያልተጀመሩ ሲኾን የጨረታ ሂደት ውስጥ እንደሚገኙም አቶ መሐመድ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!