
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የበጋ መስኖ ስንዴ በሰሜን ጎንደር ዞን በኹሉም ወረዳዎች በ1 ሺህ 649 ሄክታር ማሣ ላይ እየለማ ይገኛል።
በደባርቅ ከተማ አሥተዳደር በምቃራ ቀበሌ በገበታ ባሕር ክላስተር ስንዴን በመስኖ እያለሙ የሚገኙት አርሶ አደር አሰፋ ኀይሉ ከዚህ ቀደም ማሣቸውን ድንች፣ ምሥርና ሌሎች ሰብሎችን ያለሙበት እንደነበር ገልጸዋል። በዘንድሮው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመሩት የመስኖ ስንዴ ከዚህ ቀደም ያለሙት ከነበረው የተሻለ ውጤት እያዩበት መኾኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር አቶ ዛፉ መልካሙ ሁለት ሄክታር ማሣ በመስኖ ስንዴ ሸፍነዋል። ስንዴ በመስኖ ይለማል የሚል ግምት እንዳልነበራቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሞከረው ልማት በተሻለ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
የመስኖ ስንዴውን ከሰበሰቡ በኃላ ባቄላ በመዝራት ለሦስተኛ ጊዜ ለማልማት ማቀዳቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ መንግሥት የባቄላ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲያቀርብላቸውም ጠይቀዋል።

የስንዴ መስኖ ልማቱን በቀጣይ ዓመት በሰፊው የማልማት ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል። መንግሥት በዘንድሮው ዓመት ያጋጠሙ ችግሮችን መፍትሔ ቀድሞ እንዲያስብበትም ጠይቀዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ በምርት ዘመኑ 2 ሺህ 300 ሄክታር ማሣ በመስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ 1 ሺህ 600 ሄክታር በዘር መሸፈን እንደተቻለ አብራርተዋል። በዘር ከተሸፈነው ማሣም 70 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የመምሪያ ኀላፊው በዞኑ ለመስኖ አገልግሎት ተጀምረው በጦርነቱና በሌሎች ምክንያቶች የተቋረጡ 18 የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን ወደ ሥራ በማስገባት በዘንድሮው ዓመት ያጋጠመውን የመስኖ ልማት የውኃ እጥረት በቀጣይ እንዳይከሰት ለማድረግ እንሠራለንም ብለዋል።

በደባርቅ ከተማ ምቃራ ቀበሌ ገበታ ባህር ክላስተር በ34 ሄክታር ማሣ እየለማ የሚገኝ የመስኖ ስንዴ በዞኑ የሥራ ኀላፊዎችና አጋር ተቋማት ተጎብኝቷል።
ዘጋቢ: አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!