በአማራ ክልል የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸውን የክልሉ ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

143
ባሕርዳር:የካቲት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛው ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባዔው ሁለተኛ ቀን ሲቀጥል በአማራ ክልል የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እየተጠናቀቁ አለመኾኑን የክልሉ ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጉባዔው ላይ ገልጿል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ የተቀመጠ ቢኾንም የአፈጻጸም ተግዳሮት ገጥሟቸዋል ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል። ወይዘሮ አበራሽ ግንባታውን በተቋራጭነት የወሰዱ አካላት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ አለመግባት እና አንዳንዶችም በቦታው አለመገኘታቸው ለሥራው መጓተት ምክንያቶች መኾናቸውን በመስክ ምልከታ አረጋግጠናል ነው ያሉት። የተቋማቱ ግንባታ መጓተት የኅብረተሰቡን ጤና ጫና ውስጥ ከመክተቱም ባለፈ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄን እያስነሳ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ግንባታቸው የተጀመሩ የጤና ተቋማት በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለኅብረተሰቡ ጤና መሻሻል ግብዓት እንዲኾኑ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል። ቋሚ ኮሚቴው ተከታታይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም የተከበሩ ወይዘሮ አበራሽ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው አጥረው የሚያስቀምጡ ባለሃብቶች ቁጥር መበራከቱ ኢኮኖሚውን እየጎዳ ነው”
Next articleአቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ከብሪታንያ እና ሰሜን አየርላንድ አምባሳደር ጋር ተወያዩ።