የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት 24 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት አሥመለሰ፡፡

397

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው መስፍን እንደገለፁት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ በደብረ ማርቆስ ከተማ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕንጻ ለማስገንባት ሚያዚያ ወር 2000 ዓ.ም ለፓን አፍሪካ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውል ሰጥቶ ነበር፤ ተቋራጩ ሥራውን ጀምሮ 26 ነጥብ 08 ከመቶ ከሠራ በኋላ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሊያጠናቅቅ ባለመቻሉ ውሉ ተቋርጦ ለሌላ ተቋራጭ ሲሰጥ የመጀመሪያው ውል ባለመፈጸሙ ያስከተለውን ወጭና የወሰዱትን ቅድሚያ ክፍያ ፓን አፍሪካ ኮንስትራክሽን ድርጅት እና ዋሱ አፍሪካ ኢንሹራንስ እንዲከፍሉ ክስ ተከፍቶ ነበር፡፡ ክስ ቀርቦ ከብር 14 ሚሊዮን 384 ሺህ 820 በላይ ተቋራጭና ዋስ በአንድነት እንዲከፍሉ ታኅሳስ 23/2010 ዓ.ም ተወስኖ ሳይፈጸም ቆይቶ ነበር፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጉዳዩን ከቆመበት በማንቀሳቀስ ባለእዳ የሆነው አፍሪካ ኢንሹራንስ የተወሰነበትን ገንዘብ እንዲከፍል ተጠይቆ ፈቃደኛ በመሆን የተወሰነበትን ገንዘብ ከነወለዱ ከብር 24 ሚሊዮን 411 ሺህ 260 በላይ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ የባንክ ሒሳብ ገቢ ማድረጉ ታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የተመለሰውን ገንዘብ የፋይናንስ ሥርዓቱን ተከትሎ መልሶ ሥራ ላይ እንዲያውል ለተቋሙ ማሳሰቡን የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡

Previous articleበሰሃላ ሰየምት ወረዳ የተከሰተው ድርቅ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ከማስከተሉም በላይ የመሠረተ ልማት አለመኖር የቁጥጥር ሥራውን አዳጋች አድርጎታል ተባለ፡፡
Next articleወጣቱ ከግጭት ተግባር ተቆጥቦ በፍሬያማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ስምሪት ላይ ማተኮር እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡