
ደሴ: የካቲት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው አንድ ዓመት በአንድ ቀበሌ የተጀመረው መርሐ ግብር አሁን በ12 ቀበሌዎች እንደሚተገበር ተገልጿል።
የኮምቦልቻ ከተማ ምግብ ዋስትና ሴፍትኔት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እታፈራሁ አሰግደው እንዳሉት በኮምቦልቻ ከተማ በመጀመሪያው ዙር በከተማ ልማትና በቀጥታ ድጋፍ ባለፈው አንድ ዓመት በተጀመረው ፓይለት ፕሮጀክት 1 ሺህ 485 ተጠቃሚዎች ተሳትፈዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ5ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ፣ አረንጋዴ ልማት፣ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት፣ የከተማ ግብርና እና አነስተኛ መሰረት ልማት በከተማ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎቹ የሚሠሩ ተግባራት መኾናቸውንም ኀላፊዋ አብራርተዋል።
የኮሞቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ የምግብ ዋስትና ሴፍትኔት ፕሮግራም በዋናነት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ማኀበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም በፕሮግራሙ ውስጥ የታቀፉ አባላት ከተማቸውን ጽዱ እና አረንጋዴ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከንቲባው አክለውም በተረጅነት ስሜት ሳይኾን በአጋዥነት መንፈስ እንዲሠሩም በአደራ ጭምር
ተናግረዋል።
በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ የኾኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች እንደተናገሩት የሴፍትኔት ፕሮግራሙ ከእጅ ወደ አፍ የኾነውን ኑሯቸውን ለመቀየር አግዟቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከተረጂነት ስሜት እንዳወጣቸው እና የቁጠባ ባሕላቸውን እንዳዳበረላቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!