
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሰሃላ ሰየምት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚገኙ ሰባት የገጠር ወረዳዎች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ ከዝቋላ፣ ምሥራቅ በለሳ፣ በየዳ እና አበርገሌ ወረዳዎች ጋር የምትዋሰነው ሰሃላ ሰየምት በ2011/12ዓ.ም የምርት ዘመን በተከሰተው ድርቅ 13 ቀበሌዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ ሆነውባታል፡፡
ነዋሪዎቿ ከእርሻ ባሻገር ሕይወታቸው በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ነገር ግን የተከሰተው ድርቅ በነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን አገሬው እንደ ብቸኛ አንጡራ ሀብት በሚያያቸው እንስሳቱ ላይ ሳይቀር አደጋ ደቅኗል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ በድርቅ የምትመታው ወረዳዋ የዛሬን አያድርገውና በዚህ መልኩ ተፈጥሮ ፊቷን ስታዞርባቸው የተሻሉ አጎራባች ወረዳዎች ላይ እንስሳቶቻቸውን አሽሽተው ክፉ ቀንን ያሳልፉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ከወትሮው በተለየ መልኩ ሁሉም አጎራባች ወረዳዎቻቸው ተመሳሳይ ፈተና ገጠማቸውና ክፉ ቀን የሚያሳልፉበት አማራጭ ሁሉ አጥተዋል፡፡
ድርቁ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ይዞ መጥቷል ያሉት የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሳው ፈንታየ ናቸው፡፡ ችግሩን የከፋ ያደረገው ደግሞ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በመንገድ ችግር የዕርዳታ ቁሳቁስ ለተጠቃሚው ማደያ ጣቢያ ድረስ ማድረስ አለመቻሉ መሆኑ ነው፡፡ በወረዳው ውስጥ ሦስት የማደያ ጣቢያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ከሁለቱ ማደያ ጣቢያዎች ድረስ ዕርዳታውን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ‹ለለምሶ› በሚባለው ማደያ ጣቢያ ላይ ግን ተሽከርካሪ መግባት ባለመቻሉ የዕርዳታ ቁሳቁሶችን ለተጠቃሚዎቹ ማድረስ አለመቻሉንም ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡
ከወረዳው ዋና ከተማ መሸሀ እስከ ለለምሶ ማደያ ጣቢያ ያለው የ86 ኪሎ ሜትር አካባቢ ጥርጊያ መንገድ በአፋጣኝ ካልተሠራ አረጋውያን፣ እናቶች እና ሕጻናት ከሦስት ቀን በላይ በእግር ተጉዘው ሌላ ማደያ ጣቢያ ላይ ዕርዳታ ሊወስዱ እንደሚገደዱ ነው የተገለጸው፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ወረዳው ከዓመታዊ በጀቱ አንድ ሚሊዮን ብር ለመንገድ ሥራ እና ጥገና ቢበጅትም መንገዱ በወረዳው የበጀት አቅም መሠራት ስለማይችል የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ ሊያፈላልግለት ይገባል›› ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡
የሰሀላ ሰየምት ወረዳ የወረዳውን ሕዝብ ለመቀየር እና ዓመት እስከ ዓመት የዋግን ሕዝብ ጭምር መመገብ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም የክልሉ መንግሥት የትኩረት ማነስ አካባቢውን ከችግር እንዳላወጣው ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡
ከሰባት በላይ ዓመቱን በሙሉ የማያቋርጡ ወንዞችን የታደለችው ወረዳዋ ለመስኖ፣ ለእንስሳት እርባታ፣ ለዓሳ ሀብት እና መሰል የልማት ሥራዎች ምቹ ብትሆንም የመንገድ፣ መብራት እና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አለመኖር ባለሀብቱ ወደ ወረዳዋ እንዳይገባ እና መሥራት የሚችሉት ወጣቶች እንዳይሠሩ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ የበጀት እጥረት በራስ አቅም ለመሥራት እንቅፋት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
እንደ ዘንዶ በወረዳዋ የተጠመጠመው የተከዜ ወንዝ ውኃው ለድርቅ ማስታገሻ እንኳን እንዳይውል የተባለ ይመስል ዓመቱን ሙሉ ሲፈስ እየከረም የሌሎች ሲሳይ እና የገቢ ምንጭ ከመሆን የዘለለ ለሰሃላ ሰየምት ነዋሪ ምንም ነገር አልፈየደም፡፡ በዓሳ ሀብት ልማት የተሳተፉ ወጣቶች የገበያ ትስስር አልፈጠርላቸው፤ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው በተደጋጋሚ ሞክረው እንዳተሳካላቸው አብመድ ያነጋገራቸው የመሸሀ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ ወረዳዋ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ 34 ሺህ 178 ሕዝብ የ12 ወራት ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ወረዳው በዚህ ወቅት አለኝ ከሚለው ሕዝብ ውስጥ ‹‹8 ሺህ 383 የሚሆኑት ደግሞ ከአፋጣኝ ዕርዳታ ውጪ ሆነዋል›› ሲልም ቅሬታውን ያቀርባል፤ በሚከሰተው ችግር ኃላፊነቱን እንደማይወስድ በመግለፅ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የ1998 ዓ.ም የሕዝብና ቤት ቆጠራን መነሻ ያደረገው የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ስሌት ወረዳው በተገቢው መንገድ ቆጥሬ አረጋግጨዋለሁ ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ባለመጣጣሙ ነው፡፡ ይህን መሰሉ የቁጥር አለመጣጣም ችግር በበርካታ ወረዳዎችም ይኖራል ተብሎ ይገመታልና የሚመለከተውን አካል አነጋግረን በጥቅል እናቀርባለን፡፡
ወረዳው ካለው አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ 5 ሺህ 821 ብቻ በተለያዬ መንገድ በምግብ ራሳቸውን ይችላሉ ተብሎ ተለይቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው ከመሸሀ