
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 22/2012 ዓ.ም በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚካሄደውን የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን ያዘጋጀው ‹ወንፈል› የተሰኘ የተራድዖ ድርጅት ነው፡፡ ሩጫው የተዘጋጀበት ዓላማ ድርጅቱ በአማራ ክልል ጎንደርና ባሕር ዳር ለሚያስገነባቸው የሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህር ቤቶች ገቢ ለማሰባሰብ መሆኑን የድርጅቱ ገንዘብ ያዥ ዶክተር ይንገሥ ይግዛው በስልክ ተናግረዋል፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫው ከዋሽንግተን ዲሲ በተጨማሪ በሳን ሆዜ፣ በችካጎ፣ በአትላንታ፣ በሲያትል፣ በሎሳንጀለስ፣ በሳክራመንቶ እና በሌሎች ከተሞችም በተመሳሳይ ቀን የሚደረግ ይሆናል:: ወደፊትም በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፖ ከተሞች በማስፋት ገቢ የማሰባሰብ መርሀ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ይንገሥ አስታውቀዋል፡፡ በተለያዩ ከተሞች በሚደረገው የጎና ላይ ሩጫም 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡
በገቢ ማስገኛ መርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ዶክተር ይንገሥ የተናገሩት፡፡
ወንፈል በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ የተራድዖ ድርጅት ነው፡፡ ከተመሠረተ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው በጎ አድራጎት ድርጅቱ በባሕር ዳር እና በጎንደር የሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በ2011 ዓ.ም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ እና ከአልማ ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ነበር፡፡
ወንፈል በጎንደር እና በባሕር ዳር የሚያስገነባቸውን የሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ለማጠናቀቅ 100 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹን ለማስጀመርም ከመጭው ቅዳሜ ጀምሮ መነሻ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር እንደሚያስጀምር ነው የተጠቆመው፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ