“ክልሉ ያጋጠሙትን ችግሮች በጥበብ ተሻግሮ ያቀዳቸውን ሥራዎች እንዲያሳካ ሕዝቡ ከክልሉ መንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

115
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡ ዛሬ ከሠዓት በኋላ የተጀመረው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ያቀረቡትን ያለፉት ስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል፡፡ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በጉባዔው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት በጦርነት የተጎዳውን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እንደተደረገ አብራርተዋል፡፡
በተወሰኑ አካባቢዎች እና ዘርፎች አበረታች ውጤቶች እና አፈጻጸሞች ያሉ ቢኾንም ከደረሰው ጉዳት አንጻር ጋር የሚመጣጠን ነው ማለት ግን አይቻልም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ክልሉ አሁንም ከገጠሙት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሙሉ በሙሉ አልወጣም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉን ሕዝብ የጋራ ርብርብ እና ሁለንተናዊ ድጋፍ ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በጦርነት የተጎዳውን አካባቢ መልሶ መገንባት እና ማቋቋም፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና ተደራሽነት፣ ማኀበራዊ ተቋማት ግንባታ፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ እና በርካታ ትኩረትን የሚሹ ተግዳሮቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
ክልሉ ያለበትን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኀበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ነባራዊ ኹኔታዎች ለመቀየር መሥራት ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም ነው ያሉት፡፡
በመኾኑም ውስጣዊ አንድነትን ማዕከል ያደረገ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው “ክልሉ ያጋጠሙትን ችግሮች በጥበብ ተሻግሮ ያቀዳቸውን ሥራዎች እንዲያሳካ ሕዝቡ ከክልሉ መንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ባለፉት ስድስት ወራት ከ224 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleየልፋታቸውን ውጤት እንዳገኙ የቋሪት ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡