የልፋታቸውን ውጤት እንዳገኙ የቋሪት ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

59
ባሕርዳር:የካቲት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ሞሴ ኃይሉ ቋሪት ወረዳ የዛምቢ ዝጉዳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ቀደም ሲል ቀበሌያቸው በደን የተከበበ፣ ማር እንደልብ የሚመረትበት፣ ከብቶች ጠግበው የሚገቡበት፤ መሬቱ ለም በመኾኑነ ምርት የሚታፈስበት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አርሶ አደር ሞሴ እንደሚሉት በአካባቢያቸው ያለው ደን ቀስ በቀስ እየተመነጠረና እየተመናመነ መጥቶ ተራቆተ፡፡ የሰዎች ኑሮ ከመሻሻል ይልቅ በልቶ ለማደር አስቸጋሪ ሲኾን በርካታ ሰዎች ቀያቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ ብለዋል፡፡
አርሶ አደር ሞሴ በችግሩ ዙሪያ እሳቸው እና ሌሎች የአካባቢው አዛውንቶች ከወጣቶች ጋር ተወያዩ፤ አካባቢው ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲኾን ተስማሙ፡፡ ስምምነቱን የሚጥስ ሲገኝ ደግሞ 600 ብር ሊቀጣ ተወሰነ፤ አካባቢውም የተለያዩ የዛፍ አይነቶች ተተከሉበት፤ የተቀናጀ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በተደጋጋሚ ተሠራበት፡፡ አካባባው ዛሬ አገግሞ ወደ ደንነት እየተቀየረ ነው፤ ጠፍተው የነበሩ በርካታ ሀገር በቀል ዛፎችም መታየታቸውን ነግረውናል፡፡ አርሶ አደር ሞሴ እንዳሉን በአካባቢው የሚኖሩ የተፋሰሱ ተጠቃሚዎች ሳር እያጨዱ ከብቶቻቸውን እየመገቡ ነው፡፡ በየዓመቱ በጎርፍ ይጠቁ የነበሩ የአካባቢው ሰዎች ዛሬ ለመስኖ የሚኾን ውኃ ከተራራው እያገኙ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገረመው አሳዬ ኅብረተሰቡ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የነበረው ግንዛቤ አናሳ ነበር ይላሉ፡፡ ለጊዜው የሚገኝ ጥቅም ዘላቂውን ደን እንዳወደመም ተናግረዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ለውጥ መጥቷል ይላሉ፡፡ ዛሬ ኹሉም የአካባቢው አርሶ አደሮች ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ከተሠራው አካባቢ ከብቶቻቸውን ሳር እያጨዱ እንደሚመግቡም ተናግረዋል፡፡ “እኛ የምንሠራው ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ለማስተላላፍ ነው” ብለውናል፡፡
አርሶ አደር አንሙት ሽታ በበኩላቸው አካባቢው የተጋጋጠ መሬት የነበረው ቢኾንም ዛሬ አገግሟል፡፡ “መሬታችን ምርት መሥጠት ጀምሯል በዚህም ደስተኞች ነን” ይላሉ፡፡ በሠሩት ሥራ ውጤት በማየታቸው ሥራውን እንደሚያስቀጥሉትም ነው ያስረዱት፡፡
የቋሪት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያው ተሾመ ተመስገን በወረዳው 120 ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና የውኃ እቀባ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ተራቁተው የነበሩ የወል መሬቶች እንዲያገግሙ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የአፈር ክለት መቀነስ፣ በጎርፍ ይበሉ የነበሩ አካባቢዎች ቁጥር መቀነስ፣ የምንጮች እና ወንዞች ውኃ መጨመር የተገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡ በወረዳው የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበር እየተቋቋመ መኾኑንም ነው የነገሩን፡፡ ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ተስፋየ አስማረ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራው በ15 ወረዳዎች በ387 ቀበሌዎች ላይ አየተካሄደ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የተቀናጀ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ በመሠራቱ የተራቆቱ አካባቢዎች እያገገሙ እና ወደ ቀደመ ማንነታቸው እየተመለሱ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ በ944 ተፋሰሶች 475 ሺህ ሰዎች እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡ በዘንድሮው የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ 40 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ እስካሁን በተሠሩ የተቀናጀ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራዎች ከ500 በላይ ተፋሰሶች አገግመው ከሰው እና እንስሳት ንክኪ ነፃ ኾነዋል፡፡ 196 ተፋሰሶች ደግሞ የተቀናጀ የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበር አቋቁመው ወደተጠቃሚነት ገብተዋል፡፡ በቀጣይ ሌሎች ተፋሰሶችን ወደ ዘላቂነት ለማሸጋገር ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት ሥራው ለ23 ቀናት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት በተያዘው በጀት ዓመት በዋና ዋና ሥራዎች ከ310 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ፡- በተያዘው በጀት ዓመት በ8 ሺህ 548 ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ይሠራል፡፡ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሰዎች በሥራው ላይ ይሳተፋሉ፣ እስካሁን ከ75 በመቶ በላይ ሰዎች በሥራው ላይ ተሳትፈዋል፣ በ20 ሺህ ተፋሰሶች ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው፣ በክልሉ ከ12 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ወደ ተጠቃሚነት ተሸጋግረዋል፡፡ በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች በማድለብ፣ በንብ እርባታ እና በፍራፍሬ ማልማት ሥራ ላይ ተሠማርተው ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአፈር ክለት ጋር ተያይዞ ወደ ተሻለ ውጤት የመጡ ማሳዎች እንዳሉም አቶ እስመለዓለም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ክልሉ ያጋጠሙትን ችግሮች በጥበብ ተሻግሮ ያቀዳቸውን ሥራዎች እንዲያሳካ ሕዝቡ ከክልሉ መንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን #አሚኮ