
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) የአሥተዳደር ምክር ቤቱን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉን ሁሉን ዓቀፍ የሠላም እና የሕዝብ ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም አሁንም ድረስ ያልተሻገርናቸው ችግሮች አጋጥመውናል ብለዋል፡፡
የክልሉን ሕዝብ ሠላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሚሠሩ መደበኛ የሕግ ማስከበሪያ ዘርፎች በተጨማሪ ሕዝቡ በልማዳዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶቹ ችግሮችን እንዲፈታ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡ 268 ሺህ በላይ አባላት ያላቸው 43 ሺህ የግጭት አስወጋጅ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ትርጉም ያላቸው ለውጦችን እያመጡ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው በክልሉ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንደነበር ርእሰ መሥተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡ ኮንትሮባንድ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ መዳከም ምክንያት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 224 ሚሊየን 632 ሺህ 429 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች መያዛቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!