“የሴቶች አጀንዳ የሕዝብ ጉዳይ እንዲኾን የሚሠራ ጠንካራ ማኅበር ያስፈልጋል” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

176

ባሕርዳር: የካቲት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች አጀንዳ የሕዝብ ጉዳይ እንዲኾን የሚሠራ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለዚህ ዓላማ የሚያስተባብር ጠንካራ ማኅበር እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቷ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የሴቶችን ችግር ለመፍታትና እኩልነትን ለማረጋገጥ ከተበታተነ አካሄድ ይልቅ በጋራ መሥራትን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል።

በሴቶች ላይ ከሚደርሰው የችግር አዙሪት ለመውጣት ቁልፍ ጉዳይ የሴቶች መደራጀት መኾኑን ገልጸዋል። የመብት ትግል የተናጠል ትግል ስላልኾነ ሴቶች ጠንካራ የጋራ አጀንዳ ሊይዙ ይገባል ነው ያሉት።

ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን ትስስር ለማጠናከር ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተው “የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረት “AWN” የኢትዮጵያ ቅርንጫፍን ማጠናከርና የልምድ ልውውጦችን ማጎልበት ይጠበቅብናል ብለዋል።

“ይህንን የሴቶች ወር በማስመልከት ያለፈውን እንድንገመግም፣ የዛሬውን በርትተን እንድንሠራና የወደፊቱን እንድናቅድ ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል” ሲሉም አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንቷ የምንገነባት ኢትዮጵያ ሴቶችና ታዳጊ ሴት ልጆች ሴት በመኾናቸው፣ በራሳቸው በመተማመናቸው የማይሸማቀቁባት፣ በሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተካፋይ የሚሆኑባት ፣ሃሳባቸው የሚሰማባት እንድትኾን ሁላችንም እንትጋ ብለዋል።

የሴቶች ቀን በዓመት አንድ ግዜ ብቻ የሚታወስ ሳይኾን የ365 ቀናት ሥራ መኾን አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቷ ቀኑ ያለፈውን እየኖርን ወደፊቱን ከሴቶች እኩልነት፣ ተጠቃሚነት እና ከሰው ልጅ መብት አንጻር እንድንቃኝ አስታዋሻችን ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ የገጠሙንን ችግሮች በሠላም እንዲፈቱ በትኩረት ይሠራል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next article“ባለፉት ስድስት ወራት ከ224 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)