ʺየድል ታሪክ መግለጫ፣ የነገሥታት መቀመጫ”

178
ባሕርዳር: የካቲት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እምዬ እና እቴጌ በክብር ተቀምጠውበታል፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ በግርማ ኖረውበታል፣ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ ዓለም አጫዋቾች፣ ጦረኞች ከትመውበታል። የአምባሰል ተራራዎች እንደ ታማኝ ጦረኞች በኩራት ቆመው ያስጌጡታል፤ እንደ ክብር ካባ ያስውቡታል፣ እንደ ወርቅ ጥላ ከላዩ ላይ ያለብሱታል። ትናንትም ያጅቡት ነበር፣ ዛሬም ያጅቡታል፣ ነገም እንደዚያው፡፡ እኒያ የረቀቀ ታሪክ ያላቸው፣ የከበረ ታሪክና ሃይማኖት የመላቸው ተራራዎች ግርማ እንዳለበሱት ዘመናትን ተሻግረዋል።
የአምባሰል ተራራዎችን በራስጌው፣ የሚሌን ወንዝ በግርጌው ይዞ በክብር ይኖራል፣ በረቀቀው የታሪክ መዝገብ ውስጥ ተቀርጿል፤ የሮም ነገሥታት የሚያውቁት፣ የሮም መኳንንትና መሳፍንት የተጨነቁለት፣ እቴጌ እና እምዬ ከመኳንንቶቻቸው፣ ከመሳፍንቶቻቸው፣ ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር ኾነው የመከሩበት፣ ስለ ኢትዮጵያ ክብርና ልዕልና የተወያዩበት ሥፍራ ነው፡፡
የነገሥታቱ ክብር፣ የኢትዮጵያዊነት ምስጢር፣ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት፣ አንድነት፣ ጽናት፣ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ይገለጥበታል፣ የአይደፈሬነት ታሪክ ይዘከርበታል፣ የአትንኩኝ ባይነት ልክ ይነገርበታል፡፡ ኃያላኑ ስሙን ያውቁታል፣ ስሙን እያወሱ ተወያይተውበታል ውጫሌ ይስማ ንጉሥ፡፡
ውጫሌ ይስማ ንጉሥ ዓድዋ ሲነሳ ይነሳል፣ የዓድዋ ታሪክ ሲዘከር ይዘከራል፤ ስለ እምዬ እና እቴጌ ታሪክ በተነገረ ቁጥር ስለ እርሱም ይነገራል፡፡ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ለታሪክ የታደሉ፣ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ከፍ ብለው የሚኖሩ፣ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ በማይጠፋ ቀለም ተቀርጸው በማያረጅ ብራና ላይ የሠፈሩ፡፡ ውጫሌ ይስማ ንጉሥ ከተመረጡት፣ በታሪክ ከታደሉት፣ በታሪክ ሲነሱ ከኖሩትና ከሚኖሩት ሥፍራዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡
ውጫሌ የኢትዮጵያና የጣሊያን መንግሥታት ውል የፈጸሙበት፣ በኋላም በውሉ አለመግባባት ምክንያት የከረረ ክርክር ውስጥ የገቡበት፣ ክርክሩ ከሮ ወደ ከባድ ጦርነት የገቡበት ታሪክ ከፍ አድርጎ የሚጠራት ሥፍራ ናት፡፡ የድል ታሪክ መግለጫ፣ የነገሥታት መቀመጫ ነው፤ያ በውብ ተራራዎች ጥላ ሥር የሚኖረው ሥፍራ፡፡
ምኒልክ አዋጅ ከማስነገራቸው፣ ጦር አዝምተው ከቤተ መንግሥት ከመውጣታቸው፣ በአስፈሪ ግርማ ከመገስገሳቸው፣ እቴጌ እንደ አራስ ነብር ከመቆጣታቸው፣ በተዋበ ፈረስ ተቀምጠው ለዘመቻ ከመነሳታቸው፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች በየክፍለ ሀገሩ ከመጠራራታቸው፣ በየጎራው ከመሰባሰባቸው፣ በአምባለጌ ጠላትን ከመደቆሳቸው፣ በመቀሌ ምሽግ ወራሪን ከማደባየታቸው፣ በዓድዋ ተራራ ላይ የሮምን ፀሐይ ከማጥለቃቸው፣ የቅኝ ገዢን ቅስም ከመስበራቸው፣ ጠላትን መውጫ መግቢያ ከማሳጣታቸው፣ የኢትዮጵያን ሠንደቅ በዓድዋ አናት ላይ ከፍ አድርገው ከማውለብለባቸው፣ የኢትዮጵያን የአስፈሪነት ግርማ በሮም ላይ ከማሳረፋቸው፣ የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ዜና በዓለም ላይ ከማሰራጨታቸው አስቀድሞ ውጫሌ በታሪክ ተመዝግባለች፣ ለዓድዋ ዘመቻ መነሻ ኾናለች፡፡
ኢትዮጵያ እና ጣልያን በውጫሌ ውል ፈጸሙ፡፡ ውላቸው ግን በሁለት ቋንቋዎች ሲተረጎም ፍጹም ልዩነት ነበረው፡፡ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጻሕፋቸው ከውጫሌ ውል ጠብ ያፈራችው አንቀጽ 17 በአማርኛ ትርጉሟ ʺ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣልያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” የሚል ነው ብለው ጽፈዋል፡፡ በብልኾች ሀገር ብልህ ለመኾን ያማራት ጣልያን ግን በጣልያንኛ ሌላ ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው ነበር፡፡ ይኸውም ትርጉም ʺኢትዮጵያ በጣልያን ጠባቂነት ውስጥ ነች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም በጣልያን ንጉሥ አማካኝነት ካልኾነ በቀር ከማንም የመንግሥት መሪ ጋር ሊጻጻፉም፣ ሊዋዋሉም አይችሉም” የሚል አሣሪ ሕግ ነበር፡፡
በአንድ ውል የተፈጠረው ሁለት ፍጹም የተለያየ ትርጓሜ ያለውን ጉዳይ ምኒልክን አስቆጣቸው፤ እቴጌን እንደ ነብር አደረጋቸው፣ ኢትዮጵያውያን በክብራቸው መጥቶባቸዋልና አበሳጫቸው፡፡ ይህችም ውል ዓድዋን ፈጠረች፡፡ የኢትዮጵያዊያን ጀግንነት እና አይደፈሬነት ለዓለሙ ሁሉ አሳየች፡፡ ይህች ለዓድዋ ድል መነሻ የኾነችው ውል የተፈረመችው ደግሞ በውጫሌ ይስማ ንጉሥ ነው፡፡
ውጫሌ ይስማ ንጉሥ የዓድዋ ድል ራሶች እምዬን እና እቴጌን፣ የዓድዋን ጀግኖች፣ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ የሚዘክርና ለትውልድ የሚነግር ቤተ መዝክር ተገንብቶባታል፡፡ በቤተ መዘክሩ ቅጥር ግቢ ውስጥም የእምዬ እና የእቴጌ ሐውልት ተቀርጾላቸዋል፡፡ ሌሎች ሐውልቶችም በንጉሡና ንግሥቱ ዙሪያ ይቆማሉ ተብሏል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ መስፍን መኮንን የዓድዋ ጦርነት ሲነሳ ውጫሌ ይስማ ንጉሥ ይነሳል ይላሉ፡፡ ይስማ ንጉሥ እቴጌ በውጫሌ ውል ጣልያን ባመጣችው ሀሳብ እንደማይስማሙ ሲናገሩ ʺ ንጉሥ ኾይ ይስሙኝ፣ ያዳምጡኝ፣ ይስሙ ንጉሥ!ʺ ብለው በቁጣ ለጣልያናዊው መልእክተኛ ከተናገሩት ላይ የተወሰደ ስያሜ እንደኾነ ነግረውኛል፡፡
ይስማ ንጉሥ ስምምነቱ መፍረስ የሚታወስበት፣ ኢትዮጵያ በክብሬ የመጣን አልታገስም ያለችበት የሚታወስበት፣ ክንደ ብርቱ ጀግኖች፣ ጠቢባን መሪዎች የሚታሰቡበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ድል ያመጣችበትን፣ ለጥቁር ሕዝብ ኩራት የኾነችበትን፣ የቅኝ ገዢዎችን ተስፋና ምኞት የቋጨችበትን ሥፍራ ለማዬት፣ ታሪክንም ለማጥናትና ለመመራመር የሚፈልጉ ሠዎች ሊያዩት የሚገባ ሥፍራ ነው ይሥማ ንጉሥ፡፡ የአምባሰል ተራራዎች እና አቅፈው የያዙት ታሪክም ሌላኛው የሚዘከር ሥፍራ ነው፡፡
ዓድዋን ያለ ምኒልክ እና ያለ ጣይቱ ማሰብ ክርስትናን ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እስልምናን ያለ ነብዩ ሙሐመድ እንደ ማሰብ ይቆጠራልም፡፡ ጀግኖችን እና ዋና መሪዎችን ሳናስብ ዓድዋን ማሰብም መዘከርም አይቻልም ነው ያሉኝ ኃላፊው፡፡
ይስማ ንጉሥ የታሪክ ማስተማሪያ ሠሌዳ ነው፤ የዓድዋን ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን እና ለመላው ዓለም ለማስተማር ታስቦ የተገነባ ቤተ መዘክር መኾኑንም ነግረውኛል፡፡ ይስማ ንጉሥ ትውልድ እንዲማርበት፣ ተመራማሪዎች እንዲመራመሩበት ታስቦ የተሠራ ነው ብለውኛል፡፡
ቤተ መዘክሩ ከውጫሌ ስምምነት እስከ ዓድዋ ድል ድረስ ያለውን ታሪክ ይዘክራል፡፡ የሕወሃት ታጣቂዎች በአካባቢው ባደረጉት ወረራ ጉዳት እንዳደረሱበትም ነግረውኛል፡፡ የደረሰበት ጉዳት እንዲስተካከል እና ቀሪ ሥራዎች እንዲሠሩ የታሪክ ወዳዶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ የይሥማ ንጉሥ ታሪክን ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ሊጎበኙት የሚፈልጉት ታላቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በዓድዋ ሰማይ ሥር ጠላትን ድባቅ ባይመቱ ኖሮ ዛሬ ያለው ክብር ዛሬ ላይ ባልኖረ ነበር፡፡ ቀኝ ገዢዎችም ባላፈሩ ነበር፡፡ የዓድዋን ታላቅ ገድል አለዘመከር፣ የዓድዋን ታሪክ አለማወቅና አለማሳወቅ ውድቀት ነውም ብለውኛል፡፡ የዓድዋን ታሪክ ማወቅ የሚፍልግ ሁሉ ወደ ይስማ ንጉሥ እየሄደ ታሪክን ማየት ግድ ይላል ብለዋል፡፡
የከበረውን ታሪክ ለማወቅ፣ የተዋበውን ሥፍራ ለማድነቅ ወደ አምባሰል ተራራዎች ግርጌ አቅኑ፡፡ በዚያ ሥፍራ የከበረ ታሪክ ሞልቷል፣ ወደ ተራራው አናት በወጡም ጊዜ ግሽን ደብረ ከርቤን ያያሉ፣ የደጋጎችን ምድር ይቃኛሉ፣ ከረቀቀው ታሪክ ይማራሉ፡፡ ይስማ ንጉሥ የታሪክ መግለጫ፣ የነገሥታት መቀመጫ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ አየርመንገድ የሴቶች ቀንን በማስመልከት ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ በረራ አደረገ።
Next article“በሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ የገጠሙንን ችግሮች በሠላም እንዲፈቱ በትኩረት ይሠራል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)