
ባሕርዳር:የካቲት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ጾታን ሳይሆን ሀሳብን የሚመዝን በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ የአውራምባ ማኅበረሰብ መሥራች የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ ገለጹ።
የአውራምባ ማኅበረሰብ መሥራቹ የክብር ዶክተር ዙምራ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ የፆታ እኩልነት ያስፈልጋል ሲባል አንዱ አብሮ የሚነሳው ነገር የሥራ ክፍፍል ነው። አትዮጵያ ውስጥ የጾታ ልዩነት ለሥራ ክፍፍል የማይውልበት ማኅበረሰብ አለ። በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የአውራምባ ማኅበረሰብ ወንድ ወይም ሴት መሆን አንድን ነገር ማድረግ ከመቻል ጋር ቁርኝት የለውም ብለው ያምናሉ።
በፆታ እኩልነት አምናለሁ ዘመናዊ ነኝ የሚለው ወንድ እንኳን ቀላል የሚባለውን እንጀራ ጋግር ብላችሁ ብትሰጡት እንኳን መጋገር አይፈልግም ያሉት የክብር ዶክተር ዙምራ፤ ለዚህም የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ጾታን ሳይሆን ሀሳብን የሚመዝን በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ማኅበረሰብ መፍጠር ይገባል ይላሉ። አውራምባ ማኅበረሰብ ዘንድ ሴት ሕጻናት ከወንድ ሕጻናት ጋር አንድ አይነት ጨዋታን ይጫወታሉ፤ ዕድሜዋ ለሥራ የደረሰች ሴት ሞፈር ጠምዳ ታርሳለች፣ ወንድ ሊጥ አቡክቶ እንጀራ ይጋግራል፤ ወጥ ይሠራል ብለዋል።
የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ ሴትን ተፈጥሮ በራሱ እኩል አድርጎ ፈጥሯታል የሚል አመለካከት አላቸው። ይህም ፈጣሪ ሴትን እናት ወንድን አባት አድርጎ ፈጥሯል፤ ከሁለት አንዱ ቢጎድል የሚኖር የለምና የማነስና የመላቅ ሳይሆን የእኩልነት ምሳሌ ነው ይላሉ። ሴቶች ከወንዶች እኩል ተፈጥረው እኩልነታቸውን ቀምተን ነበርና የአውራምባ ማኅበረሰብ እኩልነታቸውን መልሷል ብለዋል።
የወንዱን ሥራ ሴቷ የማትሠራው ከሆነ የሴቷን ወንዱ ካልሠራው መተጋገዝ፣ አንዱ አንዱ መደገፍ አይችልምና ሙሉነት አይታሰብም ያሉት የክብር ዶክተር ዙምራ፤ ከዚያ ይልቅ ሁሉም ሥራ የሁሉም ቢሆን ኑሮ ይቀላል ብለዋል።
እንደ የክብር ዶክተር ዙምራ ገለጻ፤የአውራም ማኅበረሰብ ሥራን የወንድ የሴት ሳይል ይሠራል። በዚህም ሴቶችን አይተናል የሚጎላቸውን አላገኘንም ነገር ግን የሰው ችሎታ የሚለያይ ነው እና የወንድም ሰነፍ የሴትም ሰነፍ ይኖራል ይህ ግን ሰው ከመሆን ጋር እንጂ ከጾታ ጋር አይገናኝም ብለዋል።
ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚፈጠር የወገብ ሕመም ያጋጥማቸዋል የሚሉት የክብር ዶክተር ዙምራ፤ በሀገራችንም ወገቧ አልጠናም እየተባለ የአራስነት ጊዜ የማገገሚያ ጊዜ እንደሆነ ይታሰባል። ነገር ግን ጉዳቱ ቀላል አይደለምና ለረጅም ጊዜ ሥራ መርጣ መሥራት እንዳለባት የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሴቶችን አለመቻል ተደርጎ የሚታይ ሲሆን ነገር ግን በአውራምባ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለመቻል ሳይሆን የሚበልጠውን ፣የሚያደክመውን ሥራ ሠርታለችና በዚህ አትችይም ልትባል አይገባም ሲሉ የክብር ዶክተር ዙምራ ገልጸዋል።
በአውራምባ ማኅበረሰብ ውስጥ የሰው ችሎታ በጾታ ሳይሆን በሀሳቡ ይመዘናል። ይህም በሀሳብ የበላይነት የሚያምን፣ በመተዛዘን፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ የሚኖር ማኅበረሰብን መፍጠር ተችሏል።
የክብር ዶክተር ዙምራ እንደሚሉት፤ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ከሥራ ክፍፍል ባለፈ በዋንኛነት በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ማኅበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል። ይሄን ማሳካት ከተቻለም የልጆቻችንን ሕይወት ብሩህ ማድረግ ይቻላል። ሥራና ንግግር ካልተጣጣመ ቅዠት ነውና የሚወራውን ከሚተገብር አውራምባ ማኅበረሰብ ሌላው ማኅበረሰብ ሊማር ይገባል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!