
ባሕርዳር:የካቲት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የዕቅድና ፕሮግራም አስተዳደር ኀላፊ አቢይ ጸጋየ እንደገለጹት፥ ተቋሙ በመንገድ፣ ውኃ እና ህንጻ ፕሮጀክቶች ላይ ደረጃውን የጠበቀ የግንባታ ሥራ፣ ቁጥጥር፣ የጥናትና ዲዛይን እንዲሁም የማማከር አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

ባለፉት ሥድሥት ወራትም 3 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 343 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፣ ቁጥጥር፣ ጥናት፣ ዲዛይን እና የማማከር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም 934 ሚሊየን ብር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 93 ነጥብ 77 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
የጸጥታ ችግር፣ የፋይናንስ እጥረት እና የግብዓት ዋጋ መናር ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ያደረጉ ተግዳሮች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በተለይም በየጊዜው የሚስተዋለው የግንባታ እቃዎች ዋና ጭማሪ ለፕሮጀክቶች መዘግየት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አስረድተዋል፡፡
የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ለዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!