የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በባሕርዳር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን ጎበኙ።

110
ባሕርዳር: የካቲት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 1/2015 ዓ.ም የሚካሄደውን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛው ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባዔውን ለመካፈል ወደ ባሕርዳር ከተማ የገቡ የምክር ቤት አባላት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እየጎበኙ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላት በባሕር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይ፣ አማራ ብረታ ብረት ፋብሪካ እና የተገጣጣሚ ሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን ዘመናዊ ድልድይ ከጎበኙ የምክር ቤት አባላት መካከል የተከበሩ መካሽ አያሌው እንደገለጹት የድልድዩ የሥራ ፍጥነት ለሌሎች ጅምር ፕሮጀክቶች ዓርአያነት ያለው ነው ብለዋል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመስኖ፣ የመንገድ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በጊዜ እንዲጠናቀቁ አስፈጻሚ አካላትን የመቆጣጠር ሥራ እናከናውናለን ብለዋል። ሕዝቡ ለልማቶች ተባባሪ እንዲኾንም እንሠራለን ነው ያሉት።
ሌላው የምክር ቤት አባል የተከበሩ ንጉሤ ብርሃኑ በዘመናዊነቱ እና በርዝመቱ በኢትዮጽያ ቀዳሚ ኾኖ የሚገነባውን ድልድይ መጎብኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። የሥራ ፍጥነቱ የሚደነቅ ሥለመኾኑም ተናግረዋል። በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የመልካም አሥተዳደር ችግር እየፈጠሩ በመኾኑ ከዓባይ ድልድይ የሥራ አፈጻጸም ልምድ በመውሰድ በቶሎ እንዲጠናቀቁ ክትትል እንደሚደረግም ገልጸዋል።
May be an image of 9 people and outdoors
የተከበሩ ወይዘሮ መሰረት እሸቴ የዓባይ ድልድይ ግንባታ የሚሠራበት ቴክኖሎጅ ለክልሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ግብዓት እንደሚኾን ተናግረዋል። በቀጣይም ለሕዝብ ጥቅም የሚሰጡ እንዲህ አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በስፋት እንዲሠሩ የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የዓባይ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጅነር ፍቅረስላሴ ወርቁ ለምክር ቤት አባላት እንደገለጹት 94 በመቶ የሚኾነው የድልድዩ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ሰኔ 8/2015 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ይኾናልም ብለዋል። ድልድዩ ለቀጣይ መቶ ዓመታት አገልግሎት በሚሰጥ ጥራት እየተገነባ እንደሚገኝም ኢንጅነሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ ለአዲሱ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አስተላለፉ።
Next articleየተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።