
ባሕርዳር:የካቲት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አመልድ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ከ7 መቶ ሺህ በላይ የሚኾኑ ወገኖችን ተደራሽ የሚያደርግ ፕሮጀክቶች ይፋ አድርጓል።
አመልድ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል የማኅበረሰብን አቅም ለማሳደግ የሚሠራ ተቋም ነው። የክልሉ ማኅበረሰብ የኑሮ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ በትኩረት ይሠራል። አመልድ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ማኅበረሰብ ተኮር የኾኑ ፕሮጀክቶችን ሲተገብርም ቆይቷል።
ወጣቶችን በፖሊሲ ቀረጻ በማሳተፍ፣ በሕፃናት ላይ ለሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የመብት ጥሰቶች ጥብቅና እንዲቆሙ የማድረግ ፕሮጀክት ትውውቅ አካሂዷል።
ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል በአራት ወረዳዎች የሚተገበር ነው፣ ደሃና፣ ስናን፣ ጃዊ እና ሊቦከምከም ወረዳዎች ደግሞ ፕሮጀክቱ ሚተገበርባቸው ወረዳዎች ናቸው። ወረዳዎች የተመረጡት የገንዘብ ድጋፍ ባደረገው ዩኒሴፍ ፍላጎት እና ችግሩ በስፋት የሚስተዋልባቸው በመኾናቸው ነው ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ለዘጠኝ ወራት ይቆያል። ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ ዩኒሴፍ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ለዘጠኝ ወራት የሚቆየው ፕሮጀክት 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለታል። በፕሮጀክቱ ትውውቁ የተገኙ ተሳታፊዎች ፕሮጀክቱ የሚቆይበት ጊዜ ካለው ችግር እና ተደራሽ ከሚያደርገው ሕዝብ ብዛት አንፃር ያንሳል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተጨማሪ መጤ ልማዶችንም መከላከል እና መቆጣጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መሥራት ይገባል ተብሏል።
የደሃና ወረዳ ሴቶችና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሠረት አምባቸው በወረዳው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። አሁን ይፋ የኾነው ፕሮጀክት ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካሪ ውባለም እስከዚያ ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት በተሠሩ ሥራዎች መሻሻሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ነገር ግን በክልሉ አሁንም በሚፈለገው ልክ መቀነስ አለመቻሉንም ገልጸዋል። ከተማዎች ላይ ሣይቀር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። በመኾኑም በአመልድ ኢትዮጵያ ይፋ የኾነው ፕሮጀክት ቸግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።
በአመልድ ኢትዮጵያ የሥርዓተ ጾታ ፣ የአካል ጉዳት ማካተትና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክተር ታደሰ ዘበአማን የፕሮጀክት ትውውቁ ለፈፃሚ አካላት ግልጽ ለማድረግ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ በክልሉ የሚስታዋሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን፣ የሕጻናትን ጥቃት ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችል ሥራ ለመሥራትና ችግሮችን ለመቅረፍ መኾኑንም ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ በዘጠኝ ወራት ቆይታው 7 መቶ 18 ሺህ ወገኖችን ተደራሽ ያደርጋል ነው የተባለው። ለፕሮጀክቱ ተፈፃሚነት ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቱን ውጤታማ ማድረግ ከዩኒሴፍ ጋር የሚኖርን ግንኙነት እንደሚጨምር እና ሌሎች አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
አመልድ ኢትዮጵያ ይፋ የሚያደርጋቸውን ፕሮጀክቶች በብቃት እንደሚፈጸምም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!