
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኬሚካል ግዥው መጓተት አብያተ መንግሥታቱ በፍጥነት ጥገና እንዳይደረግላቸው እንቅፋት እንደፈጠረ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሕንጻዎች መሠረታዊ ጥገና ሳይደረግላቸው ለረጅም ዓመታት በመቆየታቸው ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በ2011 ዓ.ም የተሰነጣጠቁትን የሕንጻ አካላት ጥገና ለማድረግና የተጎዱ “የባልኮኒ” እንጨቶችን ለመቀየር እንቅስቃሴ ቢደረግም ወደ ተግባር በመግባት ሕንጻዎቹን ከጉዳት መታደግ አልተቻለም፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳድር ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ እድሳቱ ያልተከናወነው በግዥ መጓተት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለግንባታው የሚያስፈልጉ የእንጨት እና ሌሎች ቁሳቁሶች መዘጋጅታቸውን የተናገሩት ኃላፊው የሚቀየሩት “የባልኮኒ” እንጨቶች በፈንገስ እንዳይጠቁ ማከም ያስፈልጋቸዋል፤ መድኃኒቱ በጨረታ የማይገኝ በመሆኑና የምርምር ማዕከላት ቀምመው በቀጥታ ትዕዛዝ የሚያቀርቡት ስለሆነ በፋይናንስ ሕጉ መሠረት ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያትም በ2011 ዓ.ም ሳይጠገኑ ለቀሩት አብያተ መንግሥታት በዚህ ዓመትም የጥገና መዘግየት ተፈጥሮባቸዋል፡፡
የከተማ አስተዳድሩ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር መምሪያ የግዥና ንብረት አስተዳድር ቡድን መሪ አቶ ሙሐቤ ሙላቴ ‹‹ችግሩ የተፈጠረው ግዥውን ያዘዘው የጎንደር ከንቲባ በቀጥታ እንዲገዛለት ከመጠየቅ ይልቅ በፋይናንስ አሠራሩ ይፈጸም ብሎ በማቅረቡ ነው›› ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ በፋናንስ አሠራሩ ክፍተት በሚፈጠር መጓተት በቅርሶች ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከሚደርስ ሕጉ ባይፈቅድም ቀጥታ ግዥ እንዲፈጸም እንደተወሰነ ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኖራው በቀጥታ ግዥ እንዲቀርብ መደረጉን እና ኬሚካሉም በቀጥታ ግዥ እንዲቀርብ መወስኑን አስታውቀዋል፡፡
ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ጥገናው በተሻለ መልኩ እንዲከናወን የክልሉ መንግሥት ከጎንደር ከተማ ቅርሶች ከሚሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ 70 በመቶ ሚሆነውን ለጥገና እንዲውል ወስኗል፡፡ የዞኑ ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ደግሞ ተጨማሪ 36 ሚሊዮን ብር እንዲፈቀድለት ለአማራ ክልል የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቧል፤ ጽሕፈት ቤቱም የተጠየቀውን ገንዘብ በሂደት ለማሟላት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺዋስ ደሳለኝ 36 ሚሊዮን ብሩ ለ2012 ዓ.ም ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ቅርሱ አጠቃላይ ለጥገናው ከተጠየቀው በላይ እንደሚያስፈልገውም አሳውቀዋል፡፡ ጽሕፈት ቢቱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የተሰበሰበውን ብር ለጥገና እንደሚልክም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተሰበሰበውን ገንዘብ በየጊዜው በመላክ ዓመቱን ሙሉ ጥገናው የሚከናወን ይሆናል፡፡ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የ6122 ‹‹A›› አጭር የጽሑፍ መልዕክትን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለቅርሶች ጥበቃና ጥገና ድጋፍ እያሰባሰበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ምንም እንኳን መምሪያው በ2013 ዓ.ም ጥገናውን ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢይዝም በሕንጻዎቹ ላይ ከደረሰው ጉዳት እና የገንዘብ እና የግብዓት እጥረት አንጻር ጊዜ የሚጠይቅ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጥቃቅን የጥገና ሥራዎች በመደበኛ በጀት ሲከናወኑ እንደቆዩም አመልክተዋል፡፡ በቅርቡም የፋሲል ግንብ አጥር እና የመዋኛ ገንዳ ዕድሳቱ መጀመሩንና በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሆነ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ