“አልሞ ተኳሹ፣ የካራማራው ጀግና- አሊ በርኬ!”

789

“ጠላትን ቆጣሪ ልክ እንደኮርኬ
ታንክ ማራኪ ጀግና አሊበርኬ”

ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእጅ ቦንብ የጠላንትን ታንክ ላንቃ ያዘጋ፣ ታንክ ማራኪ ፣በካራማራ የድል ኒሻን ፣የሻለቃ ባሻ መዓረግም ተሸላሚ ነው – አሊ በርኬ ። የካራማራን የድል ታሪክ ስናወሳ አሊን አንረሳም።

ካራ ማራ በወርኃ የካቲት ሀገር በጠላት ስትፈተን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ዳግማዊ ዓድዋን ያነበሩበት የተራራው ሥር ንስሮች የድል ታሪክ ነው።

መቼም ኢትዮጵያ ጠላት ተኝቶ አያድርላትም። ግን ደግሞ በየዘመኑ ከየአቅጣጫው የመጣን እብሪተኛ አደብ የሚያስገዙ፣ የእሳት ቀለበት ውስጥ አስገብተው ጠላትን የሚያነዱ ትንታግ ልጆች ቸግሯት አያውቅም።

“ካራማራ” እብሪተኛው የሶማሊያው ወራሪ ሲያድ ባሬ ጦር በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ትንታጎች በእሳት ተለብልቦ ድል የተደረገበት የድል ታሪክ ምስክር ነው፣ ዳግማዊ ዓድዋ ይሉታል ጻሕፍት።

በእንግሊዝም ኾነ በጣሊያን ጫማ ተረግጣ አሳሯን ስታይ የነበረችው የዛሬዋ ሶማሊ ላንድ፣ በ1952 “ብሪቲሽ ሶማሊያ ላንድ” እና “ኢጣሊያን ሶማሊ” እድል ቀንቷቸው ከቅኝ ግዛት ነጻ ወጡ።

በዚህ ኹነት ኢትዮጵያውያንም “እንኳን ደስ ያለሽ” ባዮች ነበሩ።

ሉዓላዊነትን በነፍጥ የማስከበር ተምሳሌት፣ የአልገዛም ባይነት ነጻነት በነጻ እንደማይገኝ ማሳያዋ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ነጻነቷን ስታውጅ የሚከፋት ሀገር አይደለችምና።

ከቅኝ ግዛት ቀንበር የተላቀቀችው ሶማሊያ ሪፐብሊክ ስትመሰረትም ኢትዮጵያ ደስተኛ ነበረች። የሶማሊያ “ጎረቤት ተናካሽነት ግብሯ” የሚጀምረው ባለ አምስት ኮከብ ባንዴራ በመቅረጽ ታላቋን ሶማሊያ ለመገንባት የተነሳችበት ቅዥት ግን ለኢትዮጵያ በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አልነበረም።

ከቅኝ ግዛት የተላቀቁ ሁለቱ ግዛቶች ተዋህደው የሶማሊያ መንግስትን ሲመሰርቱ እኒያ ትናንሽ ግዛቶች ታላቋን ሶማሊያ የምናዋልደው የኬንያን ሰሜናዊ ክፍል፣ ጅቡቲንና ከኢትዮጵያ ኦጋዴንን በመጠቅለል የሶማሊያ አካል በማድረግ ነው የሚል ህልማቸው እውን ለማድረግ ህልማቸውን በካርታ ነደፉ።

ታሪካዊ ሰነዶች እንደሚያስረዱትም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በመውረር ቅዠቷ ኦጋዴንን ከመጠቅለል ባለፈም ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ላይ አጠቃላይ ሐረርጌን፣ አርሲን፣ ባሌን ሲዳማንና ከፊል ሽዋን ለመጠቅለል የሚያስችል ነበር የነደፈችው ካርታ።

አሻግራ ታላቅነቷን ለማንበር የምትከናውተው ሀገር ሶማሊያ ግን ድንገት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 15/1969 ከጉያዋ መፈንቅለ መንግሥት ተከሰተ።

በዚህም የወቅቱ ፕሬዘዳንት አብዱል ረሺድ አሊ ሸርማኪ ተገደሉ፣ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢብራሂም ኤጋል ዘብጥያ ተወረወሩ።

በወታደሩ ጀኔራል ሲያድ ባሬ የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት፣ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣኑን ተቆናጠጠ።

የሶማሊያን በትረ መንግሥት የተቆጣጠረው ሲያድ ባሬ የታላቋን ሶማሊያ ህልም ለማሳካት ግን ወደ ኋላ አላለም። በግልጽ በኢትዮጵያ ላይ ወረራን አወጀ።

ከኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ንጉሣዊ አሥተዳደርን ንዶ ወታደራዊ አሥተዳደርን ያነበረው የፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም አሥተዳደር ጠላትን ለመመከት ተዘጋጀ።
ፕሬዘዳንት መንግሥትቱ የጠላትን እብሪት ለማስትንፈስ ብቻ ሳይኾን ከነህልሙ ለመቅበር የእናት ሀገር ጥሪ አስተላለፉ።

“ተነስ! ሀገርህን፣ አብዮትህንና ሕልውናህን አድን። ተነስ ታጠቅ ፣ዝመት፣ መክት እናሸንፋለን !” አሉ ። ጥሪው ኢትዮጵያውያንን በአንድ ልብ ለአንድ ዓላማ አስነሳ፡፡ የእናት ሀገር ጥሪን ተቀብሎ ሀገርን ላለማስደፍር፣ ዳግማዊ ዓድዋን በዘመኑ እውን ለማድረግም ጀግኖች ከየመዓዘኑ ወደ ታጠቅ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ተመሙ።

ከነዚህ ትንታጎች መካከል አንድን ጀግና እናውሳ፣”አልሞ ተኳሹ ጀግና”- አሊ በርኬ።

“…ማን ይፈራል ሞት፣ ሞትን ማን ይፈራል
ለእናት ሀገር ሲባል…” የጀግኖቹ ዜማ ነበር።

ጠላት በርትቶ ድንበር ጥሶ ገባ፣ በርካታ ቦታዎችን አካለለ፣ የሐረርን ከተማ በመድፍ ቀለበት ውስጥ አስገቡ፣ድሬዳዋ አፍንጫ ስር ደረሱ፣ ይህ የጠላት ግስጋሴ ኢትዮጵያንንም ክፉኛ አስቆጣ።

የታጠቅ ትንታጎች ተነሱ፣ እግረኛው ከአየር ኀይሉ “…ሆ ብየ እመጣለሁ ሆ ብዬ በድል፣
ጥንትም የአባቴ ነው ጠላትን መግደል…” ተባለ።

በካራማራው የድል ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱ ፣ከእግረኛ ወታደሮች መካከል አልሞ ተኳሹ አሊ በርኬ አንዱ ነው።

አሊ በርኬ ውልደቱና እድገቱ በቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ ነው፡፡ አልሞ ተኳሽነትን ከአውሬ አዳኝነት እንደተለማመደ ይናገራል።
እና ሀገር በጠላት ስትወረር የእናት ሀገር ጥሪን ተቀብሎ የታሪክ አሻራውን አሳረፈ።

አሊ የእናት ሀገር ጥሪን ተከትሎ ውትድርናን ሲቀላቀል ጀምሮ ነው ትኩረት መሳብ የጀመረው።

ስልጠና ላይ ስለ አልሞተኳሽነቱ ሲያስረዳ “ስለ መሳሪያው መፍታትና መግጠም እናንተ አስተምሩኝ ፣ኢላማ መምታቱን ግን ለእኔ ተውት፣ ከፈለጋችሁ አስተምራችኋሉሁ” በማለቱ እና በተግባርም ድንቅ አልሞ ተኳሽነቱትን ሲያረጋግጥ መነጋገሪያ ኾኖ ነበር።
አሊ” አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት”የልጅነት መርሁ ነው ይባልለታል።

በእርግጥ እራሱ አሊም “አንድም ጥይት ያለ ኢላማ ተኩሼ አላዉቅም” ሲል ነው በተለያዩ ጊዜያት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጣቸው ቃለመጠይቆች የሚደመጠው።

እንዲያውም ጦር ግንባር በተሰለፈባቸው የመጀመሪያ ቀናት አንድም ጥይት ሳይተኩ መመለሱ፣ አለቃውን ያስገርመውና “አሊ እንዴት አልተኮስክም” ሲለው የሰጠው ምላሽ “ኢላማ ውስጥ የገባልኝ ጠላት አልነበረማ” የሚል ነበር።

ጓደኞቼ እኮ ዝምብለው ነው በአየር ላይ ሲተኩሱ የነበሩት ፣ለምን አንድም ጥይት መባከን የለባትም ፣አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት ነው መኾን የሚገባው ብሎ ሌላ መነጋገሪያ ኾነ።

አሊ በአንድ ቀን የውጊያ ውሎው ግን በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ የጠላት ታንኮች ወገንን ሲያሰጨንቁ አየ።
ይሄኔ ነበር አሊ በርኬ ጠላቱን አንድዶ ለመንደድ የወሰነው። በተለይ በዳካታ እና ካራማራ ግንባር የጠላት የበላይነት አይሎ ነበር። አሊ በርኬ ታንኩን በክላሽ ጥይት ደበደበው። ታንክን በጥይት እንዴት? አሊ ‘ጥይቴ አይሰራም ‘ አለ። አለቃው ሲያስረዱት ሁሉም ነገር ተገለጠለት እንጂ።

አሊ ፊት ለፊቱ እየተግተለተለ የሚመጣን የጠላት አምስት ታንክ አመድ ለማድረግ ወሰነ። በF-1 ቦንብ በተከታታይ ጥቃት አደረሰ ። ሦስቱ ሲጋዩ ቀሪዎች እርስ በርሳቸው ትርምስ ውስጥ ገቡ።

ድንገት የሶማሊያው ጦር አዛዥ ከታንክ ውስጥ ጭንቅላቱን ብቅ ሲያደርግ አሊ ‘በአንድ ጥይት ለአንድ ሰው’ መርሁ ተኮሰ፤ መታው። ረዳቱም ከአሊ አልሞ ተኳሽ አነጻጻሪ አይኖች አላመለጠም፣ እጣ ፈንታው ሞት ኾነ። አሊ በርኬ ወደ ሌላኛው ታንክ ዘለለ።

ሶማሊያዊው የታንክ ሹፌርና አሊ በርኬ ተፋጠጡ ፣ሾፌሩ የአሊን ምህረት ተማፀነ፣ አሊ በርኬ ሾፌሩን ከእነ ታንኩ አምጥቶ ለአለቆቹ አስረከበ።

የጀብዱ ጥግ በካራማራ ተራሮች ስር -አሊ በርኬ !

“ጠላትን ቆጣሪ ልክ እንደኮርኬ
ታንክ ማራኪ ጀግና አሊበርኬ” ተብሎ የተገጠመለት ጀግና አሊ በርኬ።

የትግል አጋሮቻቸው ስለ አሊ ጀብዱ ሲመሰክሩ
“የጦርነቱን መልክና ታሪክ ቀያሪ ሰው ነው” ይሉታል።
“በአሊ በርኬ ቦንብ ምርኮኛው ብዙ ነው ፣ድሉ ላይ አሊ የማይተካ አሻራ አስቀምጧል ነው የሚባልለት።

እርግጥም በዝግጅት ፣በስልጠናም በትጥቅ የበላይነትን ይዞ የመጣን ጠላት አስቀድሞ የጦር መሪን በመምታት ፣ጦርን መበትን፣ ለስኬታማ የማጥቃት ውጊያ፣ ለድልም መሰረት ማስቀመጥ፣ የአሊ በርኬ ምላጭ ሳቢ ጣቶች፣ አጣጣሪ ዓይኖች ለካራማራው የድል ፍሬ ጉልህ ሚና ነበራቸው ።

ደራሲ መቅደስ ዓቢይ በካራማራው የድል ታሪክ ጀብዱ የፈጸሙ ጀግኖችን በሚዘክረው “የካራማራ ግራሮች” መጽሐፍ የዚህን ጀብደኛ ወታደር ጀብዱ አስፍራለች።

“ጀግና፣ ቆራጥ ወታደር ግን ደግሞ ትሁት ሰው- አሊ በርኬ” ትለዋለች ደራሲዋ።

የሶማሊያው ሲያድ ባሬ ጦር ድል ተመትቶ ፣የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተከብሮ፣ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ እኒህ ጀግና ወታደር ለዚያ ወደር የለሽ ተግባሩ ከፕሬዘዳንት መንግስቱ እጅ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን ተሸልሟል። የሺሕ አለቃ ባሻነት መዓረግንም ተቀብሏል።

እንዳለመታደል ኾኖ ግን የሀገር ባለውለታው አሊ በረኬ ልክ እንደ አብዛኞቹ የያኔው ወታደሮች ሁሉ ህወሐት የመንግሥትነት መንበሩን ሲቆናጠጥ ከሚሳደዱት አንዱ ኾነ።

አሊ በርኬ በወያኔ ዘመን ወደ ኬንያ ከተሰደደበት ነገር ግን በተንኮል ወደ ሀገር እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ታስሮ በግፍ ያለፍርድ ዘጠኝ ዓመታትን በእስር ቤት እንዲያሳልፍ ተደርጓል።

ከግፍ እስራት የመፈታቱን ዜና ሲሰማ የወቅቱ ጓደኞች እንኳን ደስ ያለህ ሲሉት የሰጣቸው ምላሽ ግን አሳዛኝ ነበር “ከማረሚያ ቤት ወጥቼስ የት ነው የምሄደው? ነበር ምላሹ። ለሀገሩ የታገለው ወታደር ህልሙን ተቀምቷልና።

እንደፈራውም ከእስራት በኋላም ጎዳና ላይ ወድቋል፣ ወዛደርነትም ሠርቷል።

በእርግጥም አንዳንድ ቅን ኢትዮጵያውያን ካደረጉለት ድጋፍ ውጭ ለሀገር በከፈለው ውለታ ልክ ያልታሰበ ሰው ነው ።

መዘንጋቱ ቢያሳዝነውም ለሀገር በከፈለው ዋጋ ግን ለአፍታም እንደማይጸጸት ቃለመጠይቅ በሰጠባቸው ሚዲያዎች ሁሉ ሐቁን ይናገራል።

“ያኔ የእናት ሀገር ጥሪን ስንቀበል ዓላማችን ለሉዓላዊት ሀገር ክብር ፣ መግባቢያችንም ኢትዮጵያዊነት ነበር” ይላል አሊ።

ጀግናን ከመዘንጋት ፣ካለማክበር አባዜ ወጥቶ የሚገባውን ክብር መስጠት ግን ግድ ይላል ።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ በመስዋእትነት ሀገርን ከነ ክብሯ ላሻገሩ ጀግኖቻችን!

በጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሰማይ አልሞ የማይስተው ሚግ አብራሪ – ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ
Next article“ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮቻችን ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግሥት ምስረታ ሥራችን ካለመጠናቀቁ የመነጩ ናቸው” ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)