
ባሕርዳር: የካቲት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ አስቸጋሪ ወቅቶችን፤ በክንደ ብርቱ ልጆቿ አይበገሬነት እያለፈች እዚህ የደረሰች ማሕፀነ ለምለም ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ወሰኗን በግፍ ለመውረር ባሕር ተሻግሮ የመጣ ነጭ ጠላት በዓድዋ ጦርነት እንደጨው ተበትኖ ከተመለሰ በኋላም ኢትዮጵያን ሌላ እብሪተኛ ወራሪ አላጣትም። ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መሬት ቆርሶ በማጠቃለል ታላቋን ሶማሊያ የመመስረት ቅዤት ይዞ የተነሳው ዚያድ ባሬ በ1969 ዓ.ም መጨረሻ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተ።
በወቅቱ ኢትዮጵያ ገና በሽግግር ላይ በመኾኗ እዚህ ግባ የሚባል የጦር ኃይል አልነበራትም። ሀገሩን ለወራሪ አሳልፎ የማይሰጥ ሕዝብ ያላት ሀገር ስለመኾኗ ግን ታውቆ ያደረ ሀቅ ነው። የወቅቱ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ንጽጽር ከፍተኛ ልዩነት ያለው ነበር። ለአብነትም ሶማሊያ አራት የሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ያደራጀች ሲኾን ኢትዮጵያ ግን ምንም እንዳልነበራት ይታወቃል። ሶማሊያ 75 አየር መቃወሚያ ሚሳዔሎች የነበሯት ቢኾንም ኢትዮጵያ አንድም አልነበራትም። የተዋጊ አውሮፕላኖች ቁጥርም ቢኾን ኢትዮጵያ ሰባት ብቻ የነባሯት ሲኾን በሶማሊያ በኩል ግን 65 ነበሩ።
ይሕንን መሳሪያና በሀገር ፍቅር የሚነድ ሕዝብ ይዘው ነበር ሊቀመንበር መንግሥቱ ኅይለማርያም ሚያዚያ 4/1969 ለመላው ሕዝብ የሀገርህን አድን ጥሪ ያስተላለፉት። የእናት ሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ፊት ለፊት የገጠሙ ጀግኖች በርካታ ቢኾኑም ለዛሬ አንዱን እናነሳለን።
ይህንን ጀግና “ለሰማዩም ለምድሩም ክቡድ ነው” ይሉታል። ልቡ እንደፈቀደ የሚያዝዘውን ተዋጊ ጀት አስነስቶ፤ የጠላትን የአየር ክልል ሳይቀር ጥሶ፤ ተምዘግዝጎ እየገባ እሳት ደፍቶ የሚመለስ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበር። ለሀገሩ ነጻነት እንጅ ለራሱ ነፍስ የማይጨነቅ የጦር ገበሬ ነበር- ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ።
ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ የተወለደው በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ መራዊ ከተማ በ1944 ዓ.ም ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በመራዊ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በባሕርዳር ከተማ ጣና ሐይቅ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የተማረዉ። ኮሎኔል ታደሰ ለአብራሪነት በአየር ኃይል የተመለመለ ገና የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር። በሀገር ውስጥ እና በውጭ የአብራሪነት ስልጠናውን አጠናቅቆ በ25 ዓመቱ ጠላት የማይቀምሰው ንስር አብራሪ ኾነ።
በ1969 ዓ.ም ጀግናን የሚፈትን ነገር መጣ። የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ወረራ ፈጸመ። እንዲህ ባለ ቀን ነው ጀግና የሚፈተነው። ኢትዮጵያ በወቅቱ ለጦርነቱ ዝግጅት ያላደረገች ቢኾንም የጀግኖች ልጆቿ ልብ ግን አልተሸበረም። በተለይም አየር ኃይሉ አይቀሬውን ጦርነት እየተምዘገዘገ ገባበት።
ኮሎኔል ታደሰ ሚግ 23 የተባለውን አሜሪካን ሠራሽ ጦር አውሮፕላኑን ከድሬዳዋ አክንፎ ያስነሳና ወደበርበራ እና ሀርጌሳ ጠልቆ በመግባት የሶማሊያን ወታደራዊ ቁስ ወደአመድነት ቀይሮት ይመለስ ጀመር። የሶማሊያ ጦር ለዚህ ውጊያ ሰባት ዓመታትን በዝግጅት ስላሳለፈ እና በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ስለታጠቀ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የሞት ሞቱን ዘልቆ ሊገባ ቻለ። ከወሰኑ አልፎ 700 ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ ለሀረር እና ድሬዳዋ ከተሞች ሳይቀር አደጋ ጣለ።
“ይኽ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ፣
ከ’ራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ”
እያሉ የሚያዜሙላት ልጆቿ በዚህ ወቅትም ክንዳቸው አልዛለም። ይልቁንም ከዳር ዳር ተጠራርተው ደረታቸውን ለጦር በመስጠት ሀገር የማዳን ፍልሚያውን ተያያዙት። በዚህ ወቅት ጀግናን የሚፈትን አንድ ወታደራዊ ስልት ተነደፈ – የሶማሊያ ኃይል ሞቃዲሾ ከሚገኘው ማዘዣው እና በርበር እና ሀርጌሳ ከሚገኘው የትጥቅ እና ስንቅ ማከማቻው ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ። ለዚህም የጠላትን ክልል ጥሶ ገብቶ በሶማሊያ ውስጥ የሚገኝን አንድ ወሳኝ ድልድይ ወደ አመድነት ቀይሮ መመለስ ግድ ኾነ።
የጀግና ፈተና ብዙ ነው። ዝግጁ የኾነውን የሶማሊያ አየር መቃወሚያ ሚሳዔል አረር አልፎ ይህንን ወሳኝ ዒላማ ሊመታ የሚችል ጀግና ተፈለገ። አንዱ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ እና ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስም ለዚሁ አይቀሬ የጀግና ግዳጅ ታጩ።
ሁለቱም ልበ ሙሉ ጀግኖች የየራሳቸውን ተዋጊ አውሮፕላን አስጓርተው ወደ ጠላት ቀጠና ተምዘግዝገው ገቡ።
ኮሎኔል በዛብህ ከፊት እየመራ ገባበት። የዚያድ ባሬን የጦር ቀጠና በእሳት ያርሰው ጀመረ። የሶማሊያ ጸረ አውሮፕላን ሚሳዔል በተጠንቀቅ መቆሙን ስለገመተ ዋነኛ ዒላማ የኾነውን መሸጋገሪያ ድልድይ ለመምታት ግን አልቻለም ነበር።
ኮሎኔል ታደሰ ከኮሎኔል በዛብህ ኋላ እንደንስር እየከነፈ መጣና ወደ ተፈላጊው ድልድይ ዝቅ ብሎ በአውሮፕላኑ ሆድ የተሸከመውን አረር መድፋት ጀመረ። ድልድዩ ፍርስርሱ ወጣ።
ለመሸጋገሪያነት የሚጠቀምበት ድልድይ በንስሮቹ በመፍረሱ ወደ ኢትዮጽያ ሰርጎ የገባው የሶማሊያ ጦር ከዋና ማዘዣው ጋር የተፋታ ኾነ። ከዚህ በኋላ የኢትዮጽያ ጦርም ወራሪውን የዚያድ ባሬ ጦር በየደረሰበት ይቆላው ጀመር።
“ይኽ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ፣
ከ’ራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ”
ከጀግኖች የሀገር ልጆች አፍ የማይጠፋ ዜማ ነበር። እነ ኮሎኔል ታደሰም ወደጠላት ቀጠና ሲገቡ ሞተው ሀገርን ለማዳን እንደኾነ አያጡትም። ጀግናው ድልድዩን እንደልቡ ካደባየ በኃላ ከጠላት ሚሳዓል ግን አላመለጠም። ድልድዩን እንደሰበረ የአውሮፕላኑ አንደኛው ክንፍ ተመታበት። ጀግና የገጠመውን ብርቱ ፈተና በሚወጣበት መንገድ ይለካል።
የአውሮፕላኑ ክንፍ ሲመታ ኮሎኔል ታደሰ በጃንጥላ ወይም ፓራሹት ከሰማይ ወደ ጠላት ምድር ወረደ። በአካባቢው ያገኘውን እግረኛ የጠላት ኃይል እያለፈ ወደ ወደሚሞትላት ሀገሩ ለመግባት ታገለ። አብሮት የሄደው ኮሎኔል በዛብህ ጓደኛውን ፍለጋ ከአንድም ሁለቴ ወደ ምድር ዝቅ ብሎ እየበረረ ጓደኛውን ፍለጋ በዓይኑ አማተረ። በአራተኛው ኮሎኔል ታደሰ ያለበትን ቦታ ለማየት ቻለ። ወዲያውኑ የኢትዮጵያ ሄሊኮፕተሮች ደረሱና ኮሎኔል ታደሰን አንስተው ወደ ድሬዳዋ አመጡት።
ለሀገሩ እና ለሕዝቡ እንዲህ አይነት ውለታ የከፈለው ኮሎኔል ታደሰ በወቅቱ ከፍተኛ የሚባለውን የኅብረተሰባዊነት ኢትዮጵያ ጀግኖች ሜዳሊያ ሽልማት አግኝቷል። በ1983 ሕወሃት የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ሲያፈርስ ኮሎኔል ታደሰም ከሀገር ወጣ።
በኬንያ እና ዩጋንዱ ውስጥ እየኖረ የፓለቲካ ድርጅት በማቋቋም የሕወሃትን ሥርዓት ሲቃወም ቆይቷል። ኮሎኔሉ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን የምሕረት አዋጅ ተቀብሎ ወደሀገሩ ገብቶ ቆይቷል። በመጨረሻም ለምድር ለሰማዩ ክቡድ የኾነው ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ጥር 28 ቀን/2011 ዓ.ም በሕመም ምክንያት ሞቱ በሚወዳት ሀገሩ ኾነ።
ለካራማራ የድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ! ክብር ለጀግኖች ይሁን።
በኩር ጋዜጣ ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም ዕትም፣ የዶክተር ፈንታሁን አየለ “የኢትዮጵያ ሰራዊት ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም” የሚለውን ጽሁፍ እና ኮሎኔል ታደሰ በተለያዩ ጊዜያት የሰጧቸውን ቃለመጠይቆች በምንጭነት ተጠቅመናል።
በአሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!