
ደሴ:የካቲት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ ከሚገኙ የባንክና የኢንሹራንስ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በከተማዋ ልማት ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ደሴ ከተማ እንደ ዕድሜዋና እንደ ታሪኳ እንዲኹም እንደ ንግድ ማእከልነቷ የሚጠበቅባትን ያክል አለማደጓን ጠቅሰዋል። በመኾኑም ኹላችንም ተባብረን እድገቷን ማፋጠን አለብን ብለዋል።
“ደሴ ከተማ ከምንግዜውም በላይ የሕዝቦቿን እገዛ የምትፈልግበት ጊዜ ነው” ያሉት ከንቲባው ከተማዋ ከመንግሥት መደበኛ በጀት ውጭ በነዋሪዎቿ ርብርብ መልማት አለባት፤ ለዚህ ደግሞ ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የፋይናንስ ተቋሙና በተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሰራተኛችም በአማራ ልማት ማኅበርና መሰል መዋቅሮች ውስጥ በመሳተፍ የማኅበራዊ ዘርፉ ኀላፊነታቸው መወጣት እንዳለባቸውም ተገልጿል።

ተዋያዩቹ የአልማ አባል በመኾን ወርሀዊ ክፍያ ለመክፈል የተስማሙ ሲሆን ኅላፊዎቹ ግማሽ ደመወዛቸውን ለደሴ ከተማ ልማት ለመስጠት ተስማምተዉ ሰራተኞቻቸውንም አወያይተው ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። በቀጣይም በሚስጣቸው አቅጣጫ መሰረት ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ዘጋቢ፦ አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
