
ባሕርዳር: የካቲት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለበርካታ ችግር እንደዳረጋቸው በሰሜን ወሎ ዞን የሐራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሕዝብ መገልገያ ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎቱን ለማስጀመር እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
የሐራ ከተማ ነዋሪ አቶ መላኩ ምስጋናው ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለበርካታ ችግር እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።
ኤሌክትሪክ በመቋረጡ ምክንያት ከፍተኛ ለሆነ የውኃ ችግር ተዳርገናል። ያልተጣራ አንድ ጀሪካን ውኃ ከ35 እስከ 40 ብር እየገዛን ነው የምንጠቀመው። ይህም ከገንዘብ ኪሳራ ባለፈ ለጤናችን ጠንቅ ኾኖናል ብለዋል።
ከውኃ በተጨማሪም ወፍጮ ቤት የምናገኘው ረጅም ኪሎ ሜትር ተጉዘን ነው። የስልክ ኔትወርክ አገልግሎትም በሚፈለገው ልክ እያገኘን አይደለም። በዚህ የተነሳም ማኅበረሰቡ ምሬትና እንግልት ውስጥ ነው ያለው ብለዋል። የሚመለከተው አካል ሁሉ ችግራችንን ተመልክቶ ጊዜ ሳይሰጠው አገልግሎቱን ማግኘት እንድንችል ሊደረግ ይገባል በማለት ነው ያሳሰቡት።
ሌላኛዋ የሐራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ ሲሳይ የመብራትና የውኃ አገልግሎት ለረጅም ጊዜ በመቋረጡ ችግር ውስጥ ነው ያለነው። በከተማዋ አቅራቢያ ምንም አይነት ውኃ ባለመኖሩ ምክንያት ከ15 ኪሎ ሜትር እስከ 20 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ያልተጣራ ውኃ ነው እየተጠቀምን ያለነው ብላለች።
ከተለያዩ ቦታዎች በተሽከርካሪ ተጭኖ የሚመጣ አንድ ጀሪካን ውኃ ከ40 ብር በላይ ከፍለን ነው የምንገዛው፤ ይህ ደግሞ ለገንዘብ ኪሳራ እየዳረገን ነው ብላለች።
የሐራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድ ሰኢድ ኑር የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማኅበረሰቡን ለበርካታ ችግር ዳርጎታል ብለዋል። ውኃ፣ወፍጮ እና ሌሎች ተያያዥ ፍላጎቶችን ለማሟላት ረጅም ኪሎ ሜትር ተጉዘው እንደሚያገኙ ነው የተናገሩት።
የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ15 ቀን በፊት የኃይል አገልግሎት የጀመረ ቢኾንም በከተማዋ ያሉት 11 ትራንስፎርመሮች በጦርነቱ፣ ረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ በመቆየታቸውና ውስጣቸው ያለው ዘይት በመዘረፉ ምክንያት 10 ትራንስፎርመሮች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልኾነ አብራርተዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ከሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጋራ በመኾን ችግሩ እንዲፈታ ከዞን ጀምሮ እስከ ፌዴራል ተቋም ድረስ መጠየቃቸውን የጠቆሙት አቶ መሐመድ፤ እስካሁን ድረስ ችግሩ እንዳልተፈታና ከበፊቱ እንደባሰ ገልጸዋል።
ከተማዋ አዲስ እንደመሆኗ መጠን በርካታ ገቢዎችን መሰብሰብ የሚጠበቅባት መኾኑን ከንቲባው አንስተው፤ መብራት በመቋረጡ ምክንያት በርካታ ነጋዴዎች ከሥራ ወጪ በመኾናቸው እና ተቋማትም የሚጠበቅባቸውን ሥራ እየሠሩ ባለመኾኑ ገቢ መሰብሰብ እንዳልተቻለ ገልጸው ይህም ከተማዋ እንድትዳከም ከፍተኛ የኾነ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ሥራ አስፈጻሚ ብዙወርቅ ደምሴ ከፍተኛ የኾነ የትራንስፎርመር እጥረት ስላለ ለሕዝብ መገልገያ ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት በተያዘው ሳምንት አገልግሎቱን ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ብዙወርቅ ገለጻ፣ ችግሩ ለመፍታት የትራንስፎርመር ምደባ ተደርጓል። በቅርቡ የውኃ አገልግሎትና የጤና ተቋማት ላይ አገልግሎቱ እንዲጀምር ይደረጋል ብለዋል።
ካለው የትራንስፎርመር እጥረት የተነሳ በሐራ ከተማ ያሉትን 11ዱንም ትራንስፎርመሮች በአንድ ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረግ አይቻልም ብለዋል። ከወልዲያ ዲስትሪክት ጋር በመነጋገር ቅድሚያ ለሕዝብ ተቋማት እንደሚሰጥ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
የሐራ ከተማን መብራት ወደነበረበት ለመመለስ በኛ አቅም ብቻ አይሠራም ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ የትራንስፎርመር አቅራቢዎችን አቅም የሚጠይቅ ነው። አቅራቢዎቹ ቅደም ተከተልና ኮንትራት የተሰጣቸው ቢኾንም የተበላሸውን ለይቶ እንዲሠራ ለማድረግ ጊዜ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ያለው የኃይል አቅርቦት ችግር የተፈታ በመኾኑ የትራንስፎርመሮች ጥገና ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
