
ባሕር ዳር፡ የካቲት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ ድል ከቀሪው ዓለም ለኢትዮጵያዊያን የተለየ የሚያደርገው ነጻነታቸውን ያገኙበት ድል ሳይኾን ነጻነታቸውን ጠብቀወ የዘለቁበት ድል መኾኑ ነው፡፡ በዘመነ ቅኝ ግዛት ከ50 በላይ ይደርሱ ከነበሩት የአፍሪካ ሀገራት መካከል የቅኝ ገዥዎቹን መራር ጭቆና ያልተጋቱት ሀገራት ኢትዮጵያ እና ሊቢያ ብቻ ነበሩ፡፡
ሊቢያ የቅኝ ግዛት መራር ጭቆናን ያልቀመሰቸው በዘመኑ የአሜሪካ መሳሪያ ማከማቻ እና ሞግዚት በመኾኗ ሲኾን ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ የተባበረ ክንድ ደም እና አጥንት በተከፈለበት መስዋእትነት የተገኘ አኩሪ ነጻነት ነበር፡፡ ከዓድዋ ድል በኋላ መላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ በእርግጥም ቅኝ ገዥዎችን ታጋሎ ማሸነፍ እንደሚቻል ተሞክሮ የወሰደበት ክስተት በመኾኑ በዓለም ጥቁር ሕዝብ ዘንድ የተለየ ቅቡልነት አለው፡፡
ድሉ ሀገራዊ ድል ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፋዊ ድልም ነው ያሉት አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ በዓሉም ሀገራዊ በዓል ብቻ ሳይኾን ዓለም የምታከብረው በዓል ነው ብለዋል፡፡ ድሉን ዓለም ተቀብሎታል፤ በዓሉንም ዓለም በጋራ እንዲያከብረው የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ኅላፊነታቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ከዓድዋ ታሪካዊ ድል በኋላ ኢትዮጵያኒዝም እና ፓን-አፍሪካኒዝም የተባሉ እሳቤዎች እና ንቅናቄዎች በመላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ዘንድ እንደ መታገያ መሥመር ሲወሰዱ አይተናል ያሉት ጋዜጠኛ ጥበቡ ኢትዮጵያዊያን ድሉን በዓመት አንድ ቀን ብቻ ማክበር ሳይኾን የሀገረ መንግሥት ምስረታ እሴት ማድረግ ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡ “ዝክረ ዓድዋ በዓመት አንድ ቀን ብቻ ሳይኾን ዘላቂ ሀገራዊ እሴት እንዲኾን የብዙሃን መገናኛ ተቋማት መሥራት ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር እና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ደራሲያን እና ጋዜጠኞች ዓድዋ ላይ ብዥታ የላቸውም፡፡ ድሉን የዓለም ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ድል፣ ኢትዮጵያዊያንን የድሉ ባለቤት፣ አጼ ምኒልክን፣ እቴጌ ጣይቱን እና የጦር አበጋዞቻቸውን የድሉ ጉልላት አድርጎ በመቀበል አሁንም ድረስ እያከበሩት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን የዓድዋ ድልን ከፍታ፣ የመሪዎቹን ውለታ እና የታሪካዊን ክስተት አንደምታ በሚመጥን መልኩ በየጊዜው ለትውልዱ መቅረብ አለበት ነው ያሉት፡፡ በተለይም የብዙሃን መገናኛ ተቋማት የተዛባውን እይታ በማረቅ እና ተቀራራቢ አረዳድ እንዲኖር በትጋት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
