የጋዜጠኛው የጉዞ ማስታዎሻ ሲቀጥል፡፡

358

የጋዜጠኛው የጉዞ ማስታዎሻ ሲቀጥል፡፡

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) ‹‹ካልተቀጠቀጠ አይበላም ቋንጣ፤
የዋግ ሹሞች ሀገር ላስታና ሰቆጣ፡፡›› እያልኩ ጉዞ ላይ ነኝ፡፡

መነሻየን ከቀደምት የስልጣኔ አውራነታችን ምስክር እና ከዘመናት በፊት የጥበብ ቀንዲልነታችን አሻራ መገኛ ከሆነችው ጥንታዊቷ ሮሃ ካሁኗ ላልይበላ ላይ አድርጌ መድረሻየን ጀብዱን ከትህትና ፍቅርን ከልግስና አዋደውና አስማምተው ወደሚኖሩት ጥንታዊዎቹ የዋግ ሹሞች አገር ሰቆጣ አድርጌያለሁ፡፡

ስለጉዞየ ከማውራቴ በፊት ቃል በገባሁላችሁ መሠረት የላልይበላ ቆይታ ትዝብቴን በአጭሩ ላጋራችሁማ፡፡ ላልይበላ ውስጥ በአዘቦት ቀን ሳይቀር ድንገተኛ ምልከታ ቢያደርጉ ከሀገሬው ቁጥር የማይተናነስ ነጭ (የውጭ ሀገር ዜጋ) በከተማዋ ውስጥ ሲርመሰመስ ያስተውላሉ፡፡ ላልይበላ ውስጥ ‹‹ፀጉረ ልውጥ›› የሚለው ገላጭ ሐረግ የሚሠራ አይመስልም፡፡ በገባው ልክ ክርስቲያን ሳይል ሙስሊም፣ ነጭ ሳይል ጥቁር፣ ሴት ሳይል ወንድ፣ ልዩነት ከመለያ ያለፈ ቦታ ሳይኖረው በቀላሉ መግባባቱን ተክነውበታል፡፡ ተግባቦት ለላልይበላ ቀለል ያለ ልማድ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ይህንን የሀገሬውን ሥነ ልቦና ጎብኝዎቹም ሳይረዱት የቀሩ አይመስሉም፤ ካልገባው ይጠይቃል በገባው ልክ ይመልሳል በቃ! ነገሮች እንዲህ ቀለል ያሉ ናቸው፡፡

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የባሕልና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ አራት አስርት ዓመታትን እያስቆጠሩ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ላልይበላ ከ1520 ዓ.ም ጀምሮ በውጭ ሀገር ዜጎች ይጎበኝ እንደነበር ፖርቹጋላዊ ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በቂ ምስክር ነው፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ ጥያቄው ከተገነባ 800 ዓመታትን ያስቆጠረው እና በውጭ ሀገር ጎብኝዎች መጎብኘት ከጀመረ 500 ዓመታትን ያሳለፈው ላልይበላ ቱሪዝሙ የሀገርን ባሕል በማይበርዝ መልኩ እየሰፋ የሕዝቡን ሕይወት ምን ያክል መቀየር ችሏል የሚለው ይመስለኛል፡፡

ሌላው እንደ ወሎ ያለ በባሕል የደረጀ ሕዝብ እንደ ላልይበላ ዓይነት የዓለምን ቱሪስት ቀልብ የሚስብ ቅርስ ይዞ ዘላቂነት ያለው የሥራ ዕድል እና ከቱሪዝሙ ጋር የሚሄድ የገበያ ትስስር በብዛት ለምን መፍጠር አልተቻለም የሚለው ሊታሰብበት የሚገባ ጥያቄ መስሎኛል፡፡ ይህን ያህል የውጭ ጎብኝ የሚጎርፍበትና በክፍያ የሚጎበኝ ቅርስ እንዴት ይህንን ያህል ዘመን ተጎብኝቶ የጥገና የሚሆን ገንዘብ አጣ ብዬም ለራሴ ጠይቄያለሁ፤ መልሱን ባላገኘውም፡፡

የላልይበላ ሌላው ትዝብቴ ግን ‹‹ላልይበላ›› ትኩረት ይሻል፡፡ ከስድስት እና ሰባት ዓመታት በፊት ከባድ መኪና እንዳያልፍባቸው ‹ተከለከሉ› የተባሉ ቦታዎች ሁሉ ከባድ መኪና ሲያልፍባቸው እያስተዋልኩ ነበር፡፡ ለማንኛውም ላልይበላ ስላለ ነውና ያወራነው ለላልይበላ ትኩረት ይሻል ባይ ነኝ፤ ከሌላ ወሬያችን ግፋ ቢል ሊሆን የሚችለው ‹ነበር› ነው፤ ይህን ደግሞ በሩቁ ያድርግልን፡፡ በመጨረሻ ግን ላልይበላን መረኳት፡፡ ላልይበላ ላይ አንድ ነገር አየሁ ‹‹ጫት በከተማ መንገዶች ላይ ፈፅሞ አይቃምም›› ይህ በእርግጥም የሕዝቡን ታላቅነት ያስመሰከረ ነውና ወጣቶቹና የከተማ አስተዳደሩ በርቱ ሊባሉ ይገባል፡፡

መነሻየ የሆነው የላልይበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት ከመዳረሻየ ወቅር መስቀለ ክርስቶስ በ500 ዘመን ዕድሜ እንደሚያንስ ይነገርለታል፡፡ ሁለቱ ታሪካዊ ኪነ ሕንጻዎች ከጥንት እስከ ዛሬ የደረሰ በርካታ መመሳሰል አላቸው፡፡ ለአብነት ያክል በዕድሜ ጥንታዊነታቸው፣ በኪነ ሕንጻ ዲዛይን ፍፁም መቀራረባቸው፣ ቤተ አምልኮነታቸው እና ከወጥ አለት የተፈለፈሉ መሆናቸው ከብዙው ጥቂቱ ተመሳስሏቸው ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁለቱም በዚህ ዘመን ሳይቀር ተመሳስሎ አላቸው፤ እሱም የመፍረስ አደጋ ውስጥ የገቡ መሆናቸው ነው፡፡ ለማንኛውም የዛሬ ጉዞየ በሁለቱ ታሪካዊ እና ጥንታዊ በሆኑት ኪነ ሕንጻዎች መካከል የሚደረግ ነበር፡፡
ከመነሻየ ላስታ ሮሃ እስከ ዋግ ሹሞች መናገሻ፤ ከላልይበላ እስከ ሰቆጣ፣ ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት አጣምሮ ከያዘው የቅዱስ ላሊበላ እስከ ዛጉዌ ስርዎ መንግሥት ጠንሳሽ ዋግ ሹሞች ድረስ አልፌ አልፌ በጉዞየ አየሁት፡፡

ስለሁለቱ ኪነ ሕንጻዎች አጭር ነገር ልበላችሁ፡፡ እንደ ወሎ ምድር ሁሉ ዋግ ኽምራም የበርካታ ሰው ሠራሽ፣ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ ሀብቶች ባለቤት ነው፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ደግሞ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኝበት ስፍራ ልዩ ስሙ ‹ውቅር አባ ዮሐንስ› ይባላል፡፡ የመስቀለ ክርስቶስ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ከሰቆጣ ከተማ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ 5 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የመስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በዓፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት (ከ495-525 ዓ.ም) ከአንድ አለት ተፈልፍሎ እንደተሠራ ይነገራል፡፡ እንደነገርኳችሁ የተፈለፈለበት የድንጋይ ዓይነት እና አሠራሩ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡

በጥንታዊ ዘመን አስከሬንን አድርቆ የማስቀመጥ ጥበብ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ኢትዮጵያውያን መረጃ አጣቅሱ ዋቢ ንቀሱ ቢባሉ ከምስክሮቻቸው ውስጥ በውቅር መስቀለ ክርስቶስ ለረጂም ዘመናት በቤተ ክርስቲያኑ ምዕራባዊ አቅጣጫ የተቀመጡት የሰው ልጅ ቅሪት አካላት ናቸው፡፡ እጅግ ድንቅ እንደነበሩ አሻራቸው የሚመሰክረው ውብ የስዕል ስራዎች ዛሬ ላይ በዘመን ቆይታ እና በጥንቃቄ ጉድለት ደብዛቸው ሊጠፋ ተቃርበዋል፡፡ 1ሺህ 527 ዓመታትን ቆሞ ታሪክን የሚዘክረው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ በ1951 ዓ.ም ሙያዊ ጥናት ያልተጨመረበት ጥገና ከማግኘቱ ውጭ አስታዋሽ ሳያገኝ ዕድሜን ወንበሩ ዘመንን ብትሩ አድርጎ በአርምሞ ይታዘበናል፡፡

ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቁመቱ 11 ነጥብ 60 ሜትር እና ወርዱ 8 ነጥብ 55 ሜትር ነው፡፡ 7 ክፍሎች፣ 4 በሮች፣ 5 ደረጃዎች፣ 14 ዝግና ክፍት መስኮቶች እና 11 አምዶች ያሉት ጥንታዊ እና ማራኪ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የዓፄ ካሌብና የልጃቸው ገብረ መስቀል የክብር ዕቃዎች ማስቀመጫ እና የዋግ ሹሞች መቃብር እንደሆነም ይነገራል፡፡

በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት እና ንግሥናን ከክህነት አጣምረው ከያዙት አራት ቅዱሳን መካከል አንዱ በሆነው ቅዱስ ላልይበላ ስም የተሰየመችው ላልይበላ ቀይ ከተማ ነች፡፡ ኮረብታማ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን የተቸረችው ላልይበላ ከከተማነቷ ይልቅ ጥንታዊ ሙዝዬምነቷ ይጎላል ቢባል ይሻላል፡፡ በጥንታዊቷ ሮሃ በአሁኗ የላልይበላ ከተማ ውስጥ የከተመው የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ግንባታ ያዩ ሁሉ እፁብ ድንቅ ይላሉ፤ ልክ እንደ ቄስ ፍራንሲስ አልቫሬዝ፡፡

እንደሰንሰለት ተያይዘው የታነፁት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥበብ ፈርጥነታቸውን ላስተዋለ ሁሉ ሳይንስ በዓለሙ ላይ ሁሉ ሳይዘምን ከ800 ዓመታት በፊት መገንባታቸውን አምኖ ለመቀበል ከራሱ ጋር ይሟገታል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ በዮርዳኖስ ወንዝ ተለያይተውና በሦስት ምድብ ተከፍለው 11 ቤተ አምልኮዎች ራሳቸውን ችለው ቆመዋል፡፡ የጥበቡ ምጥቀት የሚገርመው ደግሞ መሠረታቸው ከታች ሳይሆን ከጣራቸው ላይ መሆኑን ላየ አብዝቶ መደመምን ይጋብዛል፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር የማይመሳሰሉት 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሁሌም ላያቸው አዲስና የማይገለፁ ሚስጥር ናቸው፡፡

ጉዞየ በነዚህ የዘመናት ቋሚ ምስክሮቻችን መካከል መሆኑን ሳስብ ሐሴትን ባደርግም ከነፋስ፣ ከፀሐይና ከዝናብ ጋር እየታገሉ የትናንቱን ማንነታችን የሚመሰክሩት ዕድሜ ጠገቡ የታሪክ አሻራዎቻችን ከጉዳታቸው አለመታደግ የትውሉዱን ተጠያቂነት ያጎሉታል፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመኖች ነጠብጣብ ናቸው፤ ከዳዓማት ወደ አክሱም፣ ከአክሱም ወደ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ፣ ከውቅር መስቀለ ክርስቶስ ወደ ላልይበላ፣ ከላልይበላ ወደ ጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ከጎንደር ወደ ሸዋ የተደረጉ የስልጣንም የስልጣኔም ሽግግሮች አያያዥ መስመር የላቸውም፡፡ በመካከላቸው በርካታ ክፍተት የተፈጠረባቸው አንዱየሌላውን አሻራ እንጅ ዕውቀት ያልቀሰመባቸው ይመስላሉ፤ ይኼ ትውልድ ቀደምት ነጠብጣብ ታሪኮችን መስመር አስይዞ የተሻለ የከፍታ ዘመን ያመጣ ይሆን?
ሠላም ሁኑ!

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article‹‹በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተን ዕውቅና ላገኘን የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጠን ይገባል፡፡›› የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች
Next articleየጎንደር አብያተ መንግሥታት ዕድሳት በግዥ ሥርዓቱ ችግር ምክንያት መጓተት ገጥሞታል፡፡