
ደሴ:የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እርሳቸው ዓዋጅ ባስነገሩበት፣ ከተህ ወረኢሉ ጠብቀኝ ባሉበት፣ የሀገሬ ሰው ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ፣ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ ብለው ባወጁበት፣ ወስልተህ የቀረህ ትጣላኛለህ አልምርህም ብለው ቃል በሠጡበት፣ ቃልም በተቀበሉበት ዘመን ባንኖርም፣ ዓድዋ ዘምተን ለኢትዮጵያ ክብርና ፍቅር ደም ባናፈስስም፣ አጥንት ባንከሰክስም፣ ሕይወት ባንገብርም፣ ከአባ ዳኛው ጋር ተሰልፈን ጠላትን ለመዋጋት ባንታደልም፣ በአባ ዳኛው አንደበት አይዞህ ልጀ ባንባልም፣ በእቴጌ ልሳን ባንመረቅም ዛሬ ላይ ዓዋጁን ሰምተን ወረኢሉ ላይ ከተን ውለናል።
የእምዬ አዋጅ ዛሬም ለአንድነት ይጠራል፣ ዛሬም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደርጋል፣ ኢትዮጵያን ከምንም በላይ ያስቀድማል። ኢትዮጵያ ቀድሜሽ ልሙትልሽ፣ መከራሽን ልቀበልልሽ፣ ለቅሶሽን ላልቅስልሽ፣ አንቺን ከሚከፋሽ እኔ ከፊትሽ ቀድሜ ልሰዋልሽ ይላልና። በእምዬ ዓዋጅ ሥር ሩህሩህነት፣ ደግነት፣ ጀግንነት፣ አማኝነት ፣ ታማኝነት፣ አርቆ አሳቢነት እና ድል አድራጊነት አለ።

የእምዬን እና የእቴጌን ታሪክ ለመዘከር፣ በአምባላጌ ድል ያደረጉትን፣ በመቀሌ ጠላትን ያርበደበዱትን በዓድዋ አናት ላይ ታላቁን ድል ያመጡት ጀግኖችን ድል ለማክበር ፣ ስለ ጸናች የሀገር ፍቅራቸው፣ ስለ ከበረች ታሪካቸው፣ ስለ ማትናወፅ ኢትዮጵያዊነታቸው፣ ጠላት ስለማይደፍራት ጀግንነታቸው፣ ማንም ስለማይነጥለው አንድነታቸው ለመመስከር ወረኢሉ ከተናል። እምዬን ያክል ንጉሥ ዓዋጅ አስነግረው፣ ከተህ ጠብቀኝ ብለው፣ እርዳኝ የሚል ጥሪ አቅርበው፣ የወሰለትክ አልምርህም ብለው ምለው ማን ችሎ ከቤቱ ይቀመጣል። ማንስ የእምዬን ዓዋጅ ችላ ብሎ ይቀራል። ቃሉን እየደጋገሙ፣ ዓዋጁን እያሰቡ ይሄዳሉ እንጂ።
የኃያሉን ንጉሥ ቃል አክብረን፣ የሠሩትን ታሪክ አስታውሰን፣ በልባችን አስበን፣ በአንደበታችን እየተናገርን፣ ስማቸውን እየዘከርን፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አስቀድመን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቋን ከፍ አድርገን፣ ዓድዋ፣ ዓድዋ እያልን ደጋግመን እየጠራን እምዬ እንዳሉት ወረኢሉ ላይ ከተናል። እምዬ ዛሬም በዓዋጃቸው ለአንድነት ሕዝብን ይጣራሉ ፣በሰው ልብ ዙፋን ላይ ተቀምጠው ይኖራሉ።
ምኒልክ በግርማ በታዩበት፣ በታላቅ አጀብ ባረፉበት፣ እቴጌ በኩራት በተቀመጡበት፣ መኳንንቱ እና መሣፍንቱ አምረውና ተውበው በአስፈሪ ግርማ በተመላለሱበት፣ ኢትዮጵያን ብለው የወጡ ጀግኖች ለሀገራቸው ታምነው፣ የዓዋጁን ቃል አክብረው በተሳበሰቡበት በዚያች ታላቅ ሥፍራ ተገኝቻለሁ። የታደለች ምድር ለታላቅ ታሪክ ታጨች፣ በማይጠፋ ቀለም፣ በማያረጅ ብራና ላይ ተጻፈች። የታደሉ ሥፍራዎች ለታሪክ ይታጫሉ፣ የታደሉ ሥፍራዎች ለከፍታ ይመረጣሉ፣ ከኹሉ ልቀው ስማቸውን ያስጠራሉ። በትውልድ ልብ ውስጥ ይኖራሉ።

ወረኢሉም እንደዚህ ናት። ወረኢሉ ታድላለች፣ አስቀድማ በምኒልክ ዓዋጅ ተጠርታለች፣ በምኒልክ ልብ ውስጥም ተመርጣለች፣ እነዚያ ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ ጀግኖችን በአንድ ላይ አገናኝታለች፣ የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጆች ተቀብላ በአንድነት አስተናግዳለች፣ የታላቁ ድል ዓድዋ ስም በተነሳ ቁጥር ስትነሳ ትኖራለች። የእምዬ ዓዋጅ በተነሳ ቁጥር ትወሳለች። እኒያ የሚያስቀኑ ንጉሥና ንግሥትን ተቀብላ ያሳረፈች፣ በእነርሱም ፊት የተወደደችና የተከበረች ናትና ወረኢሉ።
በጥቅምት እኩሌታ የተሰባበሰው ሠራዊት፣ በፈረስ እየሰገረ፣ በእግሩ እየመረመረ ሄዶ ዓድዋ ላይ ድል ያደረገበትን ያን ገናና በዓል ለማክበር ነበር ወረኢሉ የተገኘሁት። የዓድዋ በዓል ሲነሳ እምዬ በዓዋጅ የጠሯት፣ ወረኢሉ ከተህ ጠብቀኝ ያሉላት ሥፍራ መነሳቷና መወሳቷ አይቀርም። በዓሉም በዚያች ሥፍራ መከበሩ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው። ወረኢሉ ተቀብላ ያስተናገደቻቸው፣ ፈጣሪ ከእናንተ ጋር ይሁን ብላ የሸኘቻቸው ጀግኖች ድል አድርገው ሲመጡም አይታለች፣ ተቀብላቸውማለች። ወረኢሉ በዚያ ዘመን በታላቅ አጀብ የመጡ ነገሥታትን እንደተቀበለች ሁሉ ዛሬም ንጉሡን እና ንግሥቷን ታስባለች። ክብራቸውን እየነገረች፣ ታሪካቸውን አየዘከረች ትኖራለች።
እርሷ የኢትዮጵያዊነት ገመድ ያስተሳሰራቸው ጀግኖች፣ የሀገር ፍቅር በልባቸው ውስጥ የሚንቀለቀልባቸው ልበ ሙሉዎች፣ መሪያቸውን የሚያከብሩ ታዛዦች፣ ለማረኩት ጠላት የሚራሩ ሩህሩሆች የተሰባሰቡባት፣ የኢትዮጵያዊነት ውልና ምስጢር ከፍ ያለባት ናት። በዚያ ዘመን በእርሷ የተሰባሰቡት ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ያስባሉ፣ ኢትዮጵያዊነትን የአንድነታቸው ገመድ ያድጋሉ፣ ሠንደቃቸውን ከሕይወታቸው አስቀድመው ይጓዛሉ።

የወረኢሉ ጎደናዎች በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ አሸብርቀዋል። የኢትዮጵያን ምልክት ከፍ አድርገው ሠቅለዋል። ቀኑ የዓድዋ በዓል የሚከበርበት ነውና ምኒልክ ኪዳን ሲያደርሱበት፣ ቅዳሴ ሲያስቀድሱበት፣ ስብሐተ እግዝአብሔር ሲያደርሱበት የነበረው፣ በኋላም ወደ ዓድዋ ይዘው ከዘመቷቸው ታቦታት መካከል አንዱ እንደኾነ የሚነገርለት የደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከመንበሩ ወጥቷል። ሊቃውንቱ እያሸበሸቡ፣ ጥዑመ ዜማውን እያቀረቡ፣ ምዕምናኑ እልል እያሉ፣ እያጨበጨቡ፣ ለመረማመጃው እያነጠፉለት፣ እየሰገዱለት በታላቅ ክብር ይጓዛል። ነጋሪቱ ይጎሰማል፣ መለከቱ ይነፋል፣ እልልታው ደምቋል፣ ሽብሸባውና አጀባው ከፍ ብሏል።
ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመንበሩ የወጣው ቀኑ ሃያ ሦስት ነውና ክብረ በዓሉ ይታሰባል፣ የዓድዋ ድል የተገኘው ሰማዕቱ በሚከበርበት ቀን ነውና የእግዚአብሔርን ጠባቂነት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ተራዳዒነት ለማሰብ በየካቲት ሃያ ሦስት ቀን ከመንበሩ ይወጣል። ወደ በዓሉ መከበሪያም በአጀብ ይሄዳል። በዓድዋ የድል በዓል ቀን በወረኢሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት፣ የእምዬ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ ጥበብ የተመላበት መሪነት፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጀግንነት፣ የኢትዮጵያውያን ኃያልነት ይዘከራል።
በአንድ ሥፍራ ሃይማኖት ፣ ታሪክ፣ እሴት፣ ባሕል ይነገራል፣ ይዘከራል። የቀደመው አንድነት በዚያ ሥፍራ አሁንም ይታያል። ታቦቱ ሲወጣ ነጋሪቱ ሲጎሰም፣ እልልታው ከፍ ሲል ያ ዓዋጅ ተጠርቶ ጦረኛው ኹሉ የተሰባሰበበት ቀንን ይመስላል። ትዕይንቱ ዓመታትን ወደ ኋላ ወስዶ ታሪክን ያስተምራል፣ የእምዬን ዘመን ያሳያል።
የዚያች ከተማ ነዋሪዎች ዛሬም ንጉሣቸውን የሚቀበሉ፣ ዛሬም ለሠራዊቱ ግብዣ የሚያደርጉ ይመስላሉ። ሽርጉዱ በዝቷልና። ያን ዘመን በእዝነ ልቡናዬ እያሰብኩት በወረኢሉ ሠማይ ሥር የሚሆነውን ኹሉ ታዘብኩት። ታቦቱ በማረፊያው ኾኖ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ይከወናል፣ ታሪክም ይነገራል ይዘከራል። እምዬን እና እቴጌን ያየኋቸው፣ ድምፃቸውን እየሰማሁ የምከተላቸውም መሠለኝ። ጥቅምት እኩሌታን ያስታውሱታል፣ የዓድዋን ጉዞ ይዘክሩታል፣ የዓድዋንም ድል ያሳዩታል።ሁሉም በአንድነት የአንድነቱን በዓል ያከብራል። ሁሉም በድሉ ይኮራል፣ ይመካል። ደስም ይሰኛል።

በዓሉ በግርማ ሲከበር ዋለ። ጊዜውም ደረሰ። ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጣበት አጀብ ወደ መንበሩ ተመለሰ። በወረኢሉ ድንቅ ነገርን አየሁ። በቀጣይ እምዬ እንዳሉት ወደ ወረኢሉ ዝመቱ፣ ክተቱ፣ አንድነቱን፣ ኢትዮጵያዊነቱን፣ ጀግንነቱን፣ አይበገሬነቱን ተመልከቱ። እምዬ ባረፉበት፣ እቴጌ በተቀመጡበት ሥፍራ እናንተም እረፉበት፣ ታሪክ ተማሩበት፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አድንቁበት። አበውን እና እመውን ከፍ ከፍ አድርጉበት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
